ጥቃቱ የተፈጸመው በሰላማዊያን ሰዎች ሳይሆን በታጣቂዎች ነው – ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ

0
250

ከትላንት በስቲያ ከመቐለ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ 25 ኪ.ሜ በምትገኝ እንደርታ ወረዳ ደብረናዝሬት ቀበሌ ተቶጋግ እዳጋ ሰሉስ በምትባል መንደር ለገበያ ተሰብስቦ የነበረ ሰው በነበረበት ወቅት ተፈፅሟል የተባለው ጥቃት ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

ቶጎጋ ዕዳጋ ሰሉስ ላይ ተፈፅሟል በተባለው የአየር ድብደባ እስካሁን ቁጥራቸው ያልታወቀ ዜጎች ህይወት አልፏል፤ በርካቶችም ቁስለኛ ሆነዋል።

የአይን እማኞች ድብደባው ማክሰኞ ከቀኑ 6 ሰዓት አካባቢ ለገበያ ተሰብስቦ በነበረ ህዝብ ላይ ነው የተፈፀመው ብለዋል። በድብደባው በሰዎች ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በእንስሳት ላይም ጉዳት ደርሷል።

የአይን እማኞቹ በቅድሚ የተመታው በገበያው እንደሆነ በኃላም በቤቶች ላይ እንደነበር አስረድተዋል።

ከቦታው ጉዳት ደርሶባቸው መቐለ አይደር ሆስፒታል የገቡት 5 ሰዎች ሲሆኑ ከእነሱ መካከል አንዷ የ2 ዓመት ከአራት ወር ህፃን ትገኛለች።

ህፃኗ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ሲሆን በአሁን ሰዓት መተንፈስ ስለማትችል የመተንፈሻ ቱቦ ተገጥሞላት ይገኛል። በሌላ በኩል የህፃኗ አባት ጉዳት ደርሶበት ወደ ህክምና እንዳይገባ በወታደሮች ተከልክሏል ተብሏል።

አንድ የአይን እማኝ ደግሞ አጠገቡ ሶስት ሰዎች መሞታቸውን ገልጿል። አህዮች ጨምሮ ብዙ እንስሶችም ሞተዋል ብሏል፤ በአካባቢው ታጣቂዎች እንደነበሩ ተጠይቆ ምንም ታጣቂ አላየሁም ብሏል።

ጉዳት የደረደባቸውን ሰዎች ለማምጣት የአምቡላንስ ሹፌሮች አምስት ጊዜ ተጉዘው አይቻልም ተብለው መመለሳቸውን ገልፀዋል።

አንድ የአምቡላንስ ሹፌር ክልከላውን ያደረጉት የመከላከያ ኃይሎች እንደሆኑ ገልጾ ምክንያታቸው ፣ “የተመታው ጁንታው ነው፣ የኛ ወገን እያለ ሲያግዝ የነበረ፣ ሰላማዊ ሰው ሳይሆን ታጋይ ነው እራሱ ምግብ ፣ ጠላ፣ ወተት ሳይቀር ሲያመላልስ የነበረና ለዚህን አይገባውም” ነው ያሉን ብሏል።

ሰኔ 15 ተፈፅሟል የተባለው ድብደባ ሃውዜን ላይ የደረሰው የአውሮፕላን ድብደባ 33ኛ ዓመት ለመዘከር በክልሉ ያሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ባንኮች ዝግ ሆነው የትግራይ ሰማዕታት በሚዘከርበት ቀን ነው ክስተቱ የተፈፀመው።

የኢትዮጰያ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ በትግራይ ክልል ቶጎጋ ላይ  የደረሰውን የአየር ጥቃት አስመልክቶ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

“ጥቃቱ 10 ሰዓት ከቀትር በኃላ ተፈፀመ እንጂ 6 ሰዓት ቀትር ላይ አልተፈፀመም በዚህ ሰዓት ገበያ የለም ብለዋል” ጄኔራል ብርሃኑ።

ጄኔራል ብርሃኑ ፤ ጥቃቱ ምግበይ በተባለ ግለሰብ የሚመራ ታጣቂ ኃይል (እሳቸው ወንበዴ ኃይል) ላይ የተወሰደ እርምጃ ነው ፤ ሰላማዊ ሰው ላይ ጥቃት አልተፈፀምም ብለዋል ሲል ቪኦኤ ዘግቧል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ መከላክያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮ/ል ጌትነት አዳነ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ሃገራዊ ምርጫውን ተከትሎ ከውጭም ከውስጥም ስጋት ስለነበር ሰራዊቱ በመንግስት ትዕዛዝ መሰረት ከትግራይ ወደ ማዕከል፣ ምስራቅ፣ ምእራብና የደቡብ የሀገራችን ክፍል እንዲንቀሳቀስ ተደርጎ ነበር ብለዋል።

“ይህን ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ በየጢሻው ተደብቆ የነበረው የህወሓት ሚሊሻ ህዝቡን ሲያስገድድና ሰላማዊ እንቅስቃሴውን ሲያስተጓጉል ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

ቡድኑ ህዝቡን እያሽበረ በዚህ እቀጥላለሁ የሚል ከሆነ ዳግም በተጠናከረ መልኩ የሀይል እርምጃ እንደሚወሰድበት አስታውቀዋል። 

አውሎ ሚድያ ሰኔ 17 / 2013 ዓ.ም 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ