ከመቐለ 25 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኘዉ ቶጎጋ አከባቢ ላይ የአየር ጥቃት መፈፀሙ ተሰማ

0
249

ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ ከሆነችዉ መቐለ 25 ኪሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዉ ቶጎጋ የምትባለዉ አካባቢ ትላንት አመሻሽ ሰኔ 15 ቀን 2013 ዓ.ም በተፈፀመ የአየር ጥቃት ንጽኋን ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱን ከአከባበው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ትላንት አመሻሽ በቶጎጋ የገበያ ቀን በመኖሩ በአካባቢ በተፈፀመው ጥቃት  ለመገበያየት የወጡ ንፁሃን ዜጎች የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው  አዉሎ ሚድያ በስልክ ያገኘዉ መረጃ ያመለክታል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸዉ ንጽኋን ዜጎች የህክምና እርዳታ ለመስጠት ከዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል የተላኩ አምቡላንሶችና የጤና ባለሞያዎች በኬላዎች የሚገኙ ወታደሮች ሊያሳልፏቸዉ እንዳልቻሉና እንግልት እንደደረሰባቸዉ ስማቸዉን እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሆስፒታሉ ሰራተኞች ለአዉሎ ሚድያ በስልክ አስረድተዋል፡፡

እስካአሁን በሆስፒታሉ ደርሰዉ የህክምና እርዳታ ማግኘት የቻሉት የሁለት አመት ህጻንን ጨምሮ አምስት የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ብቻ  ናቸዉ ሲሉ የሆስፒታሉ ሰራተኞች ተናግረዋል፡፡

ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል መድረስ የቻሉት ሶስቱ የቀዶ ጥገና ህክምና የተደረገላቸዉ ሲሆን የተቀሩት በድንገተኛ ክፍል ይገኛሉ ሲሉ የሆስፒታሉ ሰራተኞች የነገሩን ሲሆን  አዉሎ ሚድያ ተጎጂዎችን በስልክ ለማነጋገር ያደረገዉ ጥረት ለጊዜዉ አልተሳካም፡፡

ጥቃቱ ከደረሰበት ቦታ ተጎጂዎች ወደ መቐለ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ለህክምና እንዳይሄዱ በመንግሰት ሀይሎች  ኬላ ላይ ክልከላ እንደተደረገባቸው ነው የሆስፒታሉ ሰራተኞች ለአውሎ ሚድያ የተናገሩት፡፡

ሰራተኘቹ እንደገለጹልን ከመቐለ ዓይደር ሪፈራል ሆሰፒታል አምቡላነሶች ይዘን ስንሂድ እኛም ወደ ቦታው እንዳንገባ ነው ክልከላ የተደረገበን ይላሉ፤  ሰራተኞች በዛን ሰአት የነበረ ሁኔታ ሲስረዱ፡፡

በተጨማሪም በሆስፒታሉ የህክምና እርዳታ እየተሰጣቸዉ ያሉት ዜጎች ከተጎጋ በሁለት ሚኒባስ የመጡ ሲሆን ኬላ ላይ ወደ ሆስፒታል አታልፉም እንደተባሉና ፤ ከዚያም ይላሉ ሰራተኞቹ ወታደሮቹ ቁስለኞቹ ህጻናትና በእድሜ የገፉ  ሰዎች እንደሆኑ ስናስረዳቸው ነው ያሳለፉን በማለት ለአውሎ አስረድተዋል፡፡

ወታደሮቹ ተጎጂዎቹን ከኬላዉ እንዲያልፉ የፈቀዱላቸዉም ፍተሻ ካደረጉ በኋላና ወጣቶች አለመሆናቸዉን ካረጋገጡ በኋላ መሆኑ ተገልፅዋል፡፡

በተጨማሪም በተጎጋ የነበሩት 11 ተጎጂዎችን የያዙ ሁለት አምቡላንሶችም ወታደሮቹ ኬላዉን በመዝጋታቸዉ ምክንያት ማለፍ አልቻሉም ተብለዋል፡፡

ትላንት አምሻሽ በአየር  በተፈፀመው ጥቃት  ለመገበያየት በወጡ ንፁሃን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳትና ዜጎችን ለማዳን  ወደ ቦታዉ ከተጓዙና እንግልት ከደረሰባቸዉ አንድ የሆነችዉንና ለደህንነቷ ሲባል ስሟ ሊጠቀስ ያልፈለገችዉ የዓይደር ሆስፒታል ነርስ የነበረዉን ሁኔታ ለአዉሎ ሚድያ በስልክ አስረድታላች፡፡

ደብደባዉ እንዳጋጠመ የዓይደር የጤና ቡድን ወደ ተጎጋ አምቡላንስ በመያዝ ቀጥታ በሚወስደዉ መንገድ ለመሄድ ጉዛቸዉን እንደጀመሩ ሰራዋት ተብሎ በሚጠራውአከባቢው በሚገኘዉ ኬላ ወታደሮች አስቁሟቸዉ እንደከለከሏቸዉ ትናገራለች፡፡

አሁንም ሌላ አማራጭ መንገድ በመጠቀም ተጎጂዎቹ ጋር ለመድረስ የተደረገዉ ጥረት እንዳልተሳካና አልዓሳ ላይ የሚገኘዉ ኬላ የማለፊያ ፍቃድ ደብዳቤ ካልያዛችሁ ማለፍ አትችሉም በማለት በድጋሚ እንደተከለከሉ ነርሷ ትገልጻለች፡፡

ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ወደ ትግራይ ጤና ቢሮ በማምራት የድጋፍ ደብዳቤ በማጻፍ ተመልሰዉ ወደ ኬላዉ ቢያመሩም የትግራይ ክልል የጊዚያዊ አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አብርሀም በላይና የክልሉ የኮማንድ ፖስት ሀላፊ ጀነራል ዮዉሀንስ ገ/መስቀል ፊርማ ያላረፈበት ደብዳቤ ተቀባይነት የለዉም ብለዉ እንደመለስዋቸዉ ነርሷ ተናግራለች፡፡

ከዚህ በኋላ ምሽት ሶስት ሰዓት ላይ ሰራዋት በሚገኘዉ ኬላ ማለፍ እንደቻሉና ኮኾሎ በሚባለዉ አካባቢ ከደረሱ በኋላ ግን ወታደሮች አምቡላንሷ በማስቆም የተጠየቁትን የድጋፍ ደብዳቤ ይዘዉ እንደመጡና የህክምና እርዳታ ለመስጠት ወደ ተጎጓ እየተጓዙ እንዳለ ቢያስረዷቸዉም ወታደሮቹ ምክንያታቸዉ እንዳልተቀበልዋቸዉ ትናገራለች፡፡

“ስልካችንን በመዉሰድ ለሰአታት አስረዉን ከምሽቱ አምስት ሰአት ላይ የኬላዉ ሀላፊ ድጋሜ ወደ እዚህ አካባቢ ድርሽ እንዳትሉ የሚል ማሳሰቢያ ከሰጡን በኋላ ለቀዉናል” ብላለች ነርሷ፡፡

የአዉሎ ሚድያ ዓይደር ሆስፒታል የሚሰሩ ሰራተኞች ጋር ደዉሎ ይህንን ዘገባ እስካሰናደበት ድረስ ባገኘዉ መረጃ የጤና ባለሞያዎቹ አምቡላንስ አዘጋጅተዉ ወደ ተጎጋ ለመሄድ ያደረጉት ጥረት አልተሳካላቸዉም፡፡

በዚህ ሰአት በደብዳቤ ፊርማቸዉን ሊያርፍበት ይገባል የተባሉ የክልሉ የስራ ሀላፊዎችን ደብዳቤ በመያዝ ሌላ ሙከራ እያደረጉ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል፡፡

የዓይን እማኞች ቶጎጋ በሚባል አካባቢ በገበያ ስፍራ የተፈጸመው ጥቃት በኢትዮጵያ አየር ኃይል እንደሆነ ቢናገሩም ሠራዊቱ ግን የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጎታል።

“የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው በሽብርተኛ ቡድኑ አባላት ላይ እንጂ፣ በሠላማዊ ሰዎች ላይ አይደለም” ሲሉ የሠራዊቱ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አውሎ ሚድያ ሰኔ 16 / 2013 ዓ.ም 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ