የአሜሪካ ዜግነታቸውን ለማግኘት አጭበርብረዋል የተባሉት ኢትዮጵያዊ ተያዙ

0
110

የአሜሪካ ዜግነታቸውን ለማግኘት ዋሽተዋል የተባሉ በጆርጂያ ግዛት ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአሜሪካ የፍትህ ዲፓርትመንት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

አቶ መዘምር አበበ በላይነህ የተባሉት የ65 ዓመት እድሜ ያላቸው ግለሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ በደርግ ዘመነ መንግሥት በነበረው ቀይ ሸብር ወቅት ተሳትፎ እንደነበራቸው አልተናገሩም ተብሏል።

በዲላ ከተማ በነበረ እስር ቤትና የማሰቃያ ቦታ ላይ በግለሰብ ደረጃ መርማሪ ሆነው እንዳገለገሉም የፍትህ መሥሪያ ቤቱ ያቀረበው ክስ ያስረዳል።

በእስር ቤቱም አቶ መዘምር በፖለቲካ እምነታቸው ምክንያት የታሰሩ ግለሰቦችን ለአካላዊ ስቃይ ዳርገዋል፤ እንዲሁም አንገላተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ክሱ እንደሚለው አቶ መዘምር የአሜሪካ ዜግነታቸውን ያገኙት በሕገ ወጥ መንገድ ነው።

ለዚህም እንደ ምክንያትነት የጠቀሰው ግለሰቡ በቀይ ሽብር መሳተፋቸው ቢታወቅ ኖሮ ዜግነትን አያገኙም ነበር ይህንንም ሆን ብለው ደብቀዋል የሚል ነው።

በተጨማሪም በፖለቲካ እምነታቸው ምክንያት ማንም ግለሰብ ላይ እንግልት አልፈፀምኩም የሚለውንም ዋሽተዋል ብሏል መግለጫው።

የሰብዓዊ ጥሰቶችን በተጨማሪ የአሜሪካ ሕግ በሚያዘው መሰረት ዜግነት የሚያገኙ ሰዎች ወንጀል ያልፈፀሙና ያልታሰሩ መሆን አለባቸው።

“የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፃሚዎች በአሜሪካ አገር የላቸውም” በማለት በፍትህ ዲፓርትመንት የወንጀሎች ጉዳይ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጊዜያዊ ረዳት ኒኮላስ ኤል ማክ ኳይድ መናገራቸው መግለጫው ላይ ሰፍሯል።

“ምንም እንኳን የተፈፀሙ ጥሰቶች ረዥም ዓመታትን ቢያስቆጥሩም የፍትህ ዲፓርትመንቱ ጥሰቶችን በአገራቸው የፈፀሙና አሜሪካም ለመግባት ማንነታቸውን የደበቁ ግለሰቦችን ፈልጎ ይቀጣል” ብለዋል።

አክለውም “አሜሪካ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተፈፀሙባቸውን ግለሰቦች ከለላ ትሰጣለች፤ እነዚህን ጥሰቶች የፈፀሙ ግለሰቦችንም ዝም የሚባልበት ሥርዓት የለም” በማለትም የሰሜን ጆርጂያ ግዛት ጊዜያዊ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኩርት አር ኤርስኪን ተናግረዋል።

“የመዘምር ሐሰትና የሠራው መጥፎ ተግባር በአስደሳች ሁኔታ አሁን ተጋልጧል። በአሁኑ ሰዓት ተጠያቂ ይሆናል። ይህንን ለማጋለጥ የሰሩ የደኅንነት አካላት፣ የሕህግ ባለሙያዎች፣ ባለስልጣላትና ሌሎችንም አካላት አመሰግናለሁ።

ፍትህ ይሰፍናል” በማለት በአላባማና ጆርጂያ የአገር ውስጥ ደኅንንት ምርመራን በበላይነት የሚመሩት ልዩ ባለሙያ ካትሪና ደብልዩ በርገር ተናግረዋል።

አቶ መዘምር ዜግነታቸውን በሕገ ወጥ መንገድ አግኝተዋል በሚል ሁለት ክሶች የቀረበባቸው ሲሆን በሁለቱም ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ በእያንዳንዱ የአስር ዓመት እስር ይጠብቃቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ዜግነታቸውም እንደሚነጠቅም መግለጫው አስፍሯል።

በአሜሪካ በአውሮፓውያኑ 2009 የተቋቋመው ማዕከል የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈፀመው፣ በጦር ወንጀሎች የተሳተፉ ወይም የተጠረጠሩ፣ የዘር ጭፍጨፋን ያካሄዱ፣ ግለሰቦችን ያሰቃዩ፣ ሆን ብለው ሰዎችን የገደሉ፣ የሴት ልጅ ግርዛትን የፈፀሙና ህፃናት ወታደሮችን የመለመሉ ግለሰቦችን ለፍርድ ያቀርባል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አውሎ ሚድያ ሰኔ 15 / 2013 ዓ.ም 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ