በትግራይ ክልል ርሃብ የለም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

0
127

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጦርነት በተጎዳችው ትግራይ ክልል ውስጥ ረሃብ አለ የሚሉ ሪፖርቶችን አስተባበሉ።

አገሪቱ ብሔራዊ ምርጫዋን ባደረገችበት በትናንትናው ዕለት በምርጫ ጣቢያ ላይ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ችግር መኖሩን አምነው ይህ ግን መንግሥት የሚፈታው ነው ብለዋል።

ስምንተኛ ወሩን ያስቆጠረው የትግራይ ጦርነት አምስት ሚሊዮን የክልሉን ነዋሪዎች የምግብ እርዳታ ፈላጊ እንዳደረጋቸው የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያስረዳል።

ከ350 ሺህ የሚበልጡ ነዋሪዎች ደግሞ በረሃብ ቋፍ ላይ መሆናቸውን በቅርቡ የወጣ ተባበሩት መንግሥታት ግምገማ ሪፖርት ያሳያል።

“በትግራይ ረሃብ የለም” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ድምፃቸውን በትውልድ ስፍራቸው ከሰጡ በኋላ ለቢቢሲዋ ካትሪን ባያሩሃንጋ ተናግረዋል።

“ችግር አለ ነገር ግን መንግሥት ይህንንም መቅረፍ ይችላል” በማለት አክለዋል።

ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ በፀጥታው ምክር ቤት ዝግ ስብሰባ ላይ በትግራይ ረሃብ አለ ብለው ነበር።

ኃላፊው በትግራይ ውስጥ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ እየተዋጋ ያለው የኤርትራ ሠራዊት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሞበታል ብለዋል።

በዚሁ ወቅትም ስለ ኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል መቼ እንደሚወጡ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ የኤርትራ ወታደሮችን ገፍታ እንደማታስወጣና ሁኔታውንም በሰላም ለማጠናቀቅ ከኤርትራ ጋር እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከአስር ቀናት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ የወጣ ኢንተግሬትድ ፉድ ሴኩሪቲ ፌዝ ክላሲፊኬሽን የተባለ ግምገማ መሰረት 350 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎች “ካታስትሮፍ” በሚባል ሁኔታ በረሃብ ቋፍ ላይ እንደሚገኙ አትቷል።

በወቅቱም የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ረሃብ የለም እንዲሁም እርዳታ እየተዳረሰ ነው ብለዋል።

ይሄው ግምገማ ተጨማሪ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች በቀውስ ላይ ወይም አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብሏል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በበኩላቸው ምግብ እያዳረሱ እንደሆነና የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች እንዳይገቡ ከልክለዋል የሚለውንም ሪፖርቶች ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

አውሎ ሚድያ ሰኔ 15 / 2013 ዓ.ም 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ