የአስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ የሀማስ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት መሰንዘሩን አሳወቀ

0
63

አስራኤል ከጋዛ ሰርጥ ተቀጣጣይ ነገሮችን ይዘው ወደ ግዛቷ ለተለቀቁ ፊኛዎች ምላሽ በግዛቲቱ ውስጥ የሚገኙ የሀማስ ይዞታዎችን ኢላማ ያደረጉ የአየር ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች።

በዚህም ዛሬ ረቡዕ ከንጋት በፊት ጋዛ ከተማ ውስጥ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።

ማክሰኞ ዕለት ጠዋት በርካታ ፊኛዎች ከጋዛ ወደ አስራኤል ተለቀው በተለያዩ ቦታዎች ላይ የእሳት ቃጠሎ ማስነሳታቸውን የአስራኤል የእሳት አደጋ መከላከያ አገልግሎት አስታውቋል።

ይህ ባለፈው ግንቦት ወር ለ11 ቀናት በሁለቱ ወገኖች በኩል የተካሄደው ውጊያ በተኩስ አቁም ከተጠናቀቀ በኋላ የመጀመሪያው ግጭት ነው።

የአሁኑ ጥቃት የተፈጸመው ማክሰኞ ዕለት በወረራ ስር ባለችው ምሥራቅ ኢየሩሳሌም ውስጥ አክራሪ አይሁዶች ሰልፍ ካካሄዱ በኋላ ጋዛን ከሚያስተዳድረው ታጣቂ ቡድን ከሀማስ በኩል ማስፈራሪያ መሰንዘሩን ተከትሎ ነው።

የአስራኤል መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ ላይ የጦር ጀቶቹ ካን ዩኒስ እና ጋዛ ከተማ ውስጥ በሀማስ የሚተዳደሩ ወታደራዊ ሰፈሮች ላይ ድብደባ ፈጽመዋል።

እነዚህ ወታደራዊ ሰፈሮች ኢላማ የሆኑት “የሽብር ተግባራት” ስለሚካሄዱባቸው መሆኑን ገልጾ፤ የአስራኤል መከላከያ ኃይል “ከጋዛ ሰርጥ በቀጠለው የሽብር ተግባር ምክንያት የጦርነት መጀመርን ጨምሮ ለሁሉም አይነት ክስተቶች ዝግጁ መሆኑን” አመልክቷል።

በተፈጸመው የአየር ጥቃት የደረሰ ጉዳት ይኖር እንደሆነ ወዲያውኑ የታወቀ ነገር የለም።

የሀማስ ቃል አቀባይ በትዊተር ገጹ ላይ ጥቃቱን ተከትሎ ባሰፈረው መልዕክት ፍልስጤማውያን “መብታቸውንና ኢየሩሳሌም ውስጥ ያሉትን ቅዱስ ቦታዎችን ለመከላከል የጀግንነት ተጋድሏቸውን ይቀጥላሉ” ሲል አስፍሯል።

የአስራኤል የእሳት አደጋ መከላከያ አገልግሎት እንዳለው ቀደም ሲል ከጋዛ በኩል የተለቀቁት ተቀጣጣይ ፊኛዎች በደቡባዊ አስራኤል ውስጥ ያሉ ማኅበረሰቦች ይዞታ በሆኑ መስኮች ላይ በያንስ 20 የእሳት አደጋዎችን አስከትለዋል።

ይህ ግጭት የተከሰተው ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በእስራኤል የ12 ዓመቱ የቤንያሚን ኔታኒያሁ አስተዳደር አብቅቶ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት የሚመራው አዲሱ ጥምር መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አውሎ ሚድያ ሰኔ 09/ 2013 ዓ.ም 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ