በሳዑዲ ዓረብያ ህጋዊ የመኖርያ ፍቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለእስር እየተዳረጉ ነው

0
108

ሳዑዲ ዓረቢያ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ መንግሥት የፀጥታ ኃይላትና ነዋሪዎች ከፍተኛ ወከባ፣ እስር እና ዝርፊያ እየደረሰባቸው ነው።

የሳዑዲ ዓረቢያ የጸጥታ ኃይላት የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸውንም የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች ቤቶች እየዘረፉ ለእስር በመዳረግ ላይ መሆናቸውን የችግሩ ሰለባ ኢትዮጵያውያን ለዶቼ ቨለ ተናግረዋል።

ቃላቸውን ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል፥ ለ8 ዓመት ያህል ጅዳ ነዋሪ እንደሆኑ የገለፁት አቶ ካልድ ሲራጅ የመኖሪያ ፈቃድ እንዳላቸው እየተናገሩ ከባለቤታቸው እና ሁለት ልጆቻቸው ጋር ለ3 ቀን ታስረው መፈታታቸውን ገልጸዋል። 

አቶ ካሊድ፥ “ቀጥታ መጡ፤ ልክ ከዝሁር በኋላ ከምሳ ሰአት በኋላ መጡ፤ ሰበሩ። ኢቃማ [ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ] አለን እያልናቸው እንኳን ሊሰሙን አልቻሉም፤…ተንጋግተው መጥተው ነው ቤቱን ሰብረው የገቡት” ብለዋል።

ከትናንትና ወዲያ አንስቶ እስከዛሬ ድረስ የጸጥታ ኃይላቱ “ሀበሻ” የሚሏቸውን ኢትዮጵያውያን ማሰርና ቤቶቻቸውን መስበር መቀጠላቸውን ነዋሪዎች አመልክተዋል። 

አቶ አሕመድ ሁሴን የተባሉ ነዋሪ ደግሞ ወከባ፣እስርና ዝርፊያው መቀጠሉን ተናግረዋል።

«ተደበደበ፤ ኅብረተሰቡ ንብረቱን ተወረሰ። ምነው ሂዱ ከተባልን ንብረታችንን እንኳን ይዘን ብንሄድ? እንኳን የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የመኖሪያ ፈቃድ ያለንም ብንሆን ወደ ሀገራችሁ ግቡ ብንባል በሰላም ብንገባ ምንአለበት እና ኅብረተሰቡ ተዘረፈ እያልን አሁንም አሁንም ኤምባሲ እየደወልን እየተናገርን ነው” ብለዋል። 

አክለውም ፥ “ሰሞኑን በሐበሻ ላይ የሚሠራው ሥራ ያለአግባብ ነው፤ ይመጣሉ፤ ቤት ይሰብራሉ፤ሰብረው ሰዉን ይወስዳሉ፤ ከዚያ ተከትሎ [ሸባብ] ወጣቱ ተከትሎ እየገባ ኅብረተሰቡ ተዘርፏል” ሲሉ ገልፀዋል። 

ሳዑዲ ዓረቢ ጅዳ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት ምክትል ቆንስል ጄኔራል አቶ ነቢዩ ተድላ የቆንስላው የሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ስለእስሩ እንዲያብራሩላቸው ትናንት መነጋገራቸውን ጠቅሰዋል።

 ኃላፊዎቹ የተለመደ የሳዑዲ ሕገወጦችን የመለየት ሥራ እንደሆነ እንደተናገሩ እና በመሀል ሕጋዊ ነዋሪዎች እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን ቆንስላው ማስረዳቱን ተናግረዋል።

አቶ ነብዩ ፥ “መንገለታታት እንደዚሁም ቤቶቻቸው ውስጥ የሳዑዲ ወታደሮች ገብተው ፍተሻ የማድረግ አይነት ነገሮች እንደደረሰባቸው ጠቅሰንላቸው፤ ይኼ ጉዳይ እንዲቆም እንደ ቆንስላ ጽ/ቤት ጠይቀናል። ይን ጉዳይ ለሚመለከተው የሳዑዲ የፖሊስ እና የደኅንነት ተቋማት እንደሚያቀርቡ ቃል ገብተውልናል” ብለዋል።

ቆንስላ ጽ/ቤቱ በጅዳና መካ፣ ጂዛን፣ መዲናና አባሃ ከተሞች እስካሁን ድረስ ከሰባት መቶ በላይ የታሰሩ ኢትዮጵያውያንን ማስፈታታቱንም ተናግረዋል።

የቆንስላ ጽ/ቤቱ የሳዑዲ የፀጥታ አስከባሪ አካላት በሳዑዲ የተለያዩ ከተሞች ላይ የመኖርያ ፈቃድ ባላቸውም ይሁን በሌላቸው ነዋሪዎች ላይ የፍተሻና የአፈሳ ርምጃ እየወሰዱ እንደሆነና ዜጎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልዕክት ማሰራጨቱ አይዘነጋም።

አውሎ ሚድያ ሰኔ 09/ 2013 ዓ.ም 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ