የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ ዝርፊያ እየፈጸመ ነው ተባለ

0
68

የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ ዝርፍያና የተለያዩ ትንኮሳዎች እየፈጸሙ ነው ተባለ፡፡

አቶ አሰፋ አዛናዉ እና ባለሃብት ፋሲል አሻግሬ በአካባቢዉ በግብርና ስራ ላይ ተሰማርተዉ የሚገኙና የአገርን ኢኮኖሚ የሚደግፉ እንዲሁም ለበርካቶች ስራ እድልን የፈጠሩ ናቸዉ፡፡ ነገር ግን የሱዳን ወታደራዊ ሃይል የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገብቶ የደከሙበትን ሰብል ሳይሰበስቡ ከቤት ንብረታቸዉ መፈናቀላቸው ለ ኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

በዚህም አርሶ አደር አሰፋ 87 በግና ፍየል እንዲሁም እስከ 120 ኩንታል ማሽላ ተወስዶብባቸዋል፡፡ ባለሃብት ፋሲል ደግሞ እስከ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረትን አጥተናል ብለዋል፡፡ ባለፈዉ አመት አርሰን ያፈራነዉን ሰብል የሱዳን ጦር በመዘርፉ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገናል ብለዋል የአካባቢዉ ነዋሪዎች፡፡

በያዝነዉ የመኸር እርሻ የማናርስ ከሆነም ችግሩ ከእኛ አልፎ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር መንግስት መፍትሔ ይስጠንም ብለዋል፡፡

ይህ አርሶ አደር ሀሩርና ቆፈኑ ሳይበግረዉ አመቱን ሁሉ በግብርና ስራ ላይ ተሰማርቶ እራሱን፣ ወገኑና አገሩን ለመመገብ የሚታትር ነዉ፡፡ ግን ለፍቶ ያረሰዉን ሰብል ሳይሰበስብ ግማሹ በእሳት ጋይቶበት፣ ከፊሉን ደግሞ በሱዳን ወታደሮች ተነጥቆ የደከመበትን ዉጤት ሳያገኝ መና መቅረታቸው ነው የተናገሩት፡፡

ይህ ብቻ አይደለም ባለሃብቱም ቢሆን የአገርን ኢኮኖሚ በማገዝ በግብርናዉ ዘርፍ ተሰማርቶ እያለ በሱዳን ወታደር ዝርፊያ ተፈፅሞበታል ነው የተባው፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ዉጭ ልካ የገቢ ምንጭ ከሚያስገኙላትና ኢኮኖሚዋን ከሚደግፉላት ዘርፎች መካከል ግብርና ቀዳሚዉ ሲሆን በኢትዮ- ሱዳን ድንበር አካባቢ የሚመረቱት የቅባት እህሎች ደግሞ የአንበሳዉን ድርሻ ይይዛሉ፡፡

እናም ለአገር ኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነዉ ይህ ለም መሬት በሱዳን እጅ መዉደቁና በአካባቢዉ የሚገኙ አርሶ አደሮች ለሁለት ተከታታይ አመታት የማያርሱ ከሆነ በአገሪቱ ላይ ምን አይነት ጫና ያስከትል ይሆን በማለት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት አቶ ያሬድ ሓይለመስቀልን ጥጣቄ ቀርቦላቸዋል፡፡

“አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ጫና እየደረሰባት እንደሚገኝ የሚገልፁት አቶ ያሬድ፣ በየቦታዉ የሚፈናቀለዉ አርሶ አደር ሲጨመርበት ደግሞ ችግሩን ከፍ ስለሚደርገዉ መንግስት ለእነዚህ አርሶ አደሮች መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል” ብለዋል፡፡

በፌደራል መንግስትና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህውሓት) በተጀመረ ጦርነት፣ ድንበር አልፎ የገባዉ የሱዳን ጦር አሁንም ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች እየገፋ እንደሚገኝ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

ለመሆኑ የሱዳን ጦር ምን ያህል ቦታ ነዉ የተቆጣጠረዉ በአካባቢዉ? ያለዉስ የፀጥታ ሁኔታ ምን ይመስላል? በማለት ጥያቄ የቀረበላቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪን አቶ ደሳለኝ ጣሰዉን የጠየቅን ሲሆን ከሁመራ ድንበር እስከ ቋራ ድረስ ያለዉና እስከ 5 መቶ ኪሎሜትር ባላ ድንበር በሱዳን ሰራዊት ቁጥጥር ስር ይገኛል ነዉ ያሉት፡፡

ከዚህ ቀደም የችግሩ ሰለባ የሆኑት አርሶ አደሮች ቁጥር 450 እንደነበሩ የሚናገሩት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ፤ አሁን ላይ የሱዳን ሰራዊት በየቀኑ የተለያዩ ትንኮሳዎችን ስለሚያደርግ በርካቶች እየተፈናቀሉ ነዉ ብለዋል፡፡

ችግሩ የዞኑና የአርሶ አደሮቹ ብቻ ሳይሆነ የአገሪቱ በመሆኑ የክልሉና የፌደራሉ መንግስት በጋራ በመሆን ለችግሩ መፍትሄ እንዲያመጡም አስተዳዳሪዉ ጠይቀዋል፡፡

ለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን ለመፍታት ምን እሰራ ይሆን ለሚለዉ ጥያቄም የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጦርነት አዋጭ ባለመሆኑ አሁንም የኢትዮጵያ ምርጫ ዲፕሎማሲ ነዉ ብለዋል፡፡

አውሎ ሚድያ ሰኔ 07/ 2013 ዓ.ም 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ