“ንጹሀንን ለጦርነት አላማ ብሎ ማስራብ ትልቅ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው” ያኔዝ ሌነርቼክ

0
122

የአሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ትናንት ትግራይ ክልልን በተመለከተ ውይይት ካካሄዱ በኋላ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

የዩኤስኤድ አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር፣ የአውሮፓ ሕብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌነርቼክ፣ የአውሮፓ ሕብረት ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይን እና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ቦሬል ናቸው በጋራ መግለጫውን ያወጡት።

አገራቱ ከውይይታቸው በኋላ ባወጡት በዚህ መግለጫ፤ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት 400 ሺህ ንጹሃን ዜጎች ወደ ረሃብ አፋፍ እና ሞት እየተገፉ ነው የሚል ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት በትግራይ የተጋረጠውን የረሃብ አደጋ ጉዳት ለመቀነስ መተግበር አለባቸው ያሏቸውን አምስት ጥሪዎችን ያቀረቡ ሲሆን የተኩስ አቁም ጥሪ ቀዳሚው ነው።

በትግራይ ውስጥ የሰብዓዊ እርዳታ ለማዳረስ ብሎም የሲቪሎችን ጥቃት ለማስቀረት ተኩስ አቁም ይደረግ ሲል በአራት ባለሥልጣናት ተፈርሞ የወጣው ይህ መግለጫ ጠይቋል።

የዩኤስኤድ ኃላፊ ሳማንታ ፓወር፤ የኖቤል ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ይህንን ጥቃት ካላስቆሙ እና የኤርትራን ሠራዊትን ካላስወጡ፤ በኢትዮጵያ የረሃብ ታሪክን በመድገም የሚታወሱ መሪ ይሆናሉ” ብለዋል።

የአሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ያቀረቡት ጥሪ በጦርነቱ እየተሳተፉ ያሉ አካላት ዓለም አቀፍ የጦርነት ሕጎችን እንዲያከብሩ የሚያሳስብ ጭምር ነው።

ይህም የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት ማስጠበቅን የሚጨምር ሲሆን “የተኩስ አቁም ተደረገም አልተደረገም ያለ ቅድመ ሁኔታ መተግበር አለበት” ሲል መግለጫው አሳስቧል። የእርዳታ ሰጪ ተቋማት ደኅንነት እንዲጠበቅም ጥሪ ቀርቧል።

ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያለውን የረሃብ አደጋ ለማስቀረት ሁሉም አካላት ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ ለማዳረስ የሚያስችል መንገድ እንዲፈጥሩ ተጠይቀዋል።

ሌላው የቀረበው ጥያቄ ከዚህ ቀደም በተገባው ቃል መሠረት የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ለቆ እንዲወጣ ለሁለቱ አገራት ጥሪ ቀርቧል።

በመግለጫው ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ በትግራይ ክልል የሚያደርገውን የእርዳታ መጠን እንዲሳድግ እና የሰዎችን ሕይወት እንዲያድን ጥሪ ቀርቧል።

የአሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ትናንት ባደረጉት የውይይት መድረክ ላይ “በአሥርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ብሎም ለማስቀረት የሚቻል የሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል የሚያሳዩ መረጃዎች ከትግራይ እየወጡ ነው” ሲሉ የአውሮፓ ሕብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌነርቼክ ተናግረው ነበር።

“ንጹሀንን ለጦርነት አላማ ብሎ ማስራብ ትልቅ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው” ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሁለት ቀናት በፊት በሰጠው መግለጫ በትግራይ ክልል ‘ረሃብ አለ’ መባሉን ማጣጣሉ ይታወሳል።

መንግሥት በክልሉ ውስጥ ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ እየተጠቀመ ነው በሚል በመገናኛ ብዙሃንም ሆነ በተለያዩ አካላት የወጡ ሪፖርቶችንም አጣጥለዋል።

ከሳምንት በፊት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም በሰጡት መግለጫ፤ በትግራይ ክልል በአንድ ዙር ለ4.5 ሚሊዮን ነዋሪዎች፣ በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዙር ደግሞ ለ4.3 ሚሊዮን ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ እንደተቻለ መናገራቸው ይታወሳል።

አውሎ ሚድያ ሰኔ 04/ 2013 ዓ.ም 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ