የማይ-ካድራ ሪፖርት በሮይተርስ

0
150

በምዕራብ ትግራይ የተከሰቱት የዘር ጭፍጨፋዎች የመጀመሪያ ዘገባዎች ከህዳር አጋማሽ በፊት ከተከዜ ወንዝ በስተ ምዕራብ 100 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ማይ ካድራ በተባለ የእርሻ ከተማ ውስጥ ነበር፡፡ የአማራ ተወላጆች በትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት እንደደረሰባቸው ሲናገሩ፤ የትግራይ ክልል ተወላጆች በበኩላቸዉ ወደ ሱዳን እንዲሰደዱ የተደረጉበት ምክንያት በአማራ ተወላጆች ላይ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ጥቃት ስለደረሰባቸዉ በህይወት የቀሩት መሰደዳቸዉ ያስረዳሉ፡፡

ሁለቱ ወገኖች የተስማሙበት ብቸኛው ነገር በመቶዎች የሚቆጠሩ መሞታቸው ነው፡፡ በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የመጀመሪያ ሪፖርቶች ስለ አመፅ ከፊል ዘገባዎችን ሰጥተዋል፡፡ ሁኖም የኢትዮጵያ መንግስት በቦታው የነበረ ሁኔታ መገናኛ መንገዶችን በጥብቅ በመዘጋቱ ፤ የስልክ መስመሮች በመቋረጡ በሁለቱ ወገኖች የተፈጠረ ግጭት በግልጽ መረጃ ለማወቅ አልተቻለም ይላል ሪፐርቱ፡፡

በመጋቢት ወር ላይ መንግስት በክልሉ ላይ በተወሰነ መልኩ ዘጋቢ እንዲገባ ተፈቀደለት፤ ጋዜጠኞቹ በቦታው ላይ የተቃጠሉ ቤቶች እንዲሁም የመቃብር ምልክቶች አይተዋል፡፡ ከማይ ካድራ እና ከሌሎች የትግራይ ከተሞች እና መንደሮች ተፈናቅለዉ በሱዳን በሚገኙ የስደተኞች ካምፖች ውስጥ ከ 120 በላይ ከሚሆኑት የትግራይ ተወላጆች እንዲሁም የአማራ ተወላጆች ሮይተርስ ቃለ መጠየቅ ማድረጉ ያስታዉሳል፡፡

ሮይተርስ ባለፉት ስድስት ወራት የሰበሰባቸውን መረጃዎች በሁለት ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ፣ በሕክምና መዝገቦች እና በሳተላይት መረጃዎች በተሰበሰቡ 44 ያልታተሙ የምስክር ወረቀቶችን አረጋግጧል፡፡

ብዝዎች በጅምላ መቃብር ነዉ የተቀበሩት ማንነታቸዉን ማወቅም አይቻልም፡፡ ሮይተርስም ሬሳዎች ተቀበሩበትን ቦታ የሚጦቁሙ በጥቁር ቀለም ምልክት የተደረገባቸዉ ታፔላዎች እንዳየ በዘገባዉ ይመሰክራል፡፡ የሟች ቤተሰቦች ፎቶ ይዘዉ መለየት ትችላላችሁ ወይ ብለዉ ይጠይቁ እንደነበር ማሩ የተባለችዋ ትናገራለች፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ሬሳዎች በዉሻ የተበሉ ሌሎቹ ደግሞ ከሶስት ቀናት በኋላ የመጡ በመሆናቸዉ መለየት አልቻልንም ትላለች፡፡

የኢትዮጵያ የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ 229 ሬሳዎች ተቆፍረዉ እንደተገኙ ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ ምን ያህል የትግራይ ተወላጆች ምን ያህል የአማራ የሚለዉን  መንግስት ያለዉ ነገር የለም፡፡ ኗሪዎች እንደሚሉት አሁንም ከወራት በኋላም የሰዎች ሬሳ እየተገኘ ነዉ ይላሉ፡፡

ከአማራ ማህበር በአሜሪካ ሮይተርስ አገኘሁት ባለዉ መረጃ የ707 የግጭቱ ሰለባ የአማራ ተወላጆች ስም ዝርዝር ለምስክርነት የተሰበሰቡ እንዳገኘ በዘገባዉ ያትታል፡፡ ከስም ዝርዝሮቹ አምስቱ ሮይተርስ ዘገባዉን ሲያጠናክር በራሴ መንገድ አረጋገጥኩኝ ያላቸዉ ናቸዉ፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኢሰመኮ የሞቱት ሰዎች 600 ሊደርሱ እንደሚችሉ ግምቱን ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡

ህዳር 1 ቀን 2013ዓ.ም በትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት መድረስ ጀመረ፡፡ አብዛኛዉ ጥቃት ሲያደርሱ የነበሩት የአማራ ልዩ ሀይሎችና የፋኖ ሚሊሻዎችም መሆናቸዉ 28 የትግራይ ተወላጆች ይመሰክራሉ፡፡

ሮይተርስ እንደሚለዉ አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች የአይን ምስክሮች ያገኛቸዉ ተፈናቅለዉ በሱዳን የተጠለሉ ናቸዉ፡፡ በዚህ ወቅት ከ60 ሺህ በላይ ከሀገሪቷ ተፈናቅለዉ ተጠልለዉ ይገኛሉ፡፡ ቢንያም ዓመደ ማርያም የትግራይ ተወላጅ ሲሆን ዳቦ በመጋገር ነበር የሚተዳደረዉ፣ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ላይ በማይ ካድራ ግጭት ሲነሳ ቤተሰቦቹን ይዞ ወደ ገጠር አካባቢ አሸሻቸዉ፡፡ በሚቀጥለዉ ቀን የራሱንና የቤተሰቦቹ አልባሳትና ጌጣጌጥ ለመሰብሰብ በባጃጅ ይኖርባት ወደ ነበረችዉ ማይ ካድራ ከተማ ሲመለስ ፋኖዎች ከባጃጁ አስወርደዉ በድንጋይና መጥረቢያ ደብድበዉት ከወገቡ በታች እንደማይንቀሳቀስ አድርገዉታል፡፡ ቢንያም ከአካል ጉዳተኞቱ በተጨማሪ ቤተሰቦቹ ይዞ አካባቢዉን ይዞ እንዲወጣ ፋኖዎቹ በማስፈራራታቸዉ በዚህ ወቅት በሱዳን እስከነ ቤተሰቦቹ ተጠልሎ ይገኛል፡፡

በማይ ካድራ ዉልደታቸዉና እድገታቸዉ ሆኖ የትግራይ ዘር ስላለባቸዉ ብቻ ከተማዋን ለቀዉ እንዲወጡ የፋኖ ሚሊሻዎች አስጠነቀቅዋቸዉ፡፡ አበሩ ኪሮስ ለሮይተርስ እንዳሉት የትግራይ ተወላጆቹ ምንም ነገር ማሰሮም ቢሆን ይዘዉ እንዳይወጡና ባዶ እጃቸዉ እንዲፈናቀሉ መደረጋቸዉና ፤ በበሮቻቸዉ “ይህ የአማራ ቤት ነዉ” ብለዉ እንደጻፉበትም ያስረዳሉ፡፡ ሮይተርስም “የአማራ ቤት” ና “ፋኖ” ሚሉ ጽህፎች በከተማዋ ቤቶች ማግኘቱ ይመሰክራል፡፡

በማይ ካድራ ደቡባዊ ክፍል ላይ የአማራ ልዩ ሀይሎችና ፋኖ በድንኳን በተሰሩ ጊዚያዊ እስር ቤቶች የትግራይ ተወላጆች አስረዋል፡፡ በቦታዉ ታስረዉ የነበሩትን አራት የአይን እማኞች እንደሚሉት በቦታዉ ትንሽ ምግብ፣ ዉሀና መድሀኒት ነዉ ያለዉ፤ በቦታዉ ያሉት ጠባቂዎች የጤና ባለሞያዎች ለመጥራት ፍቃደኛ አይደሉም፡፡ የ70 አመት ባለጸጋ የሆኑት አቶ ወልዴ መረሳ እንደሚሉት በቦታዉ ለሁለት ወራት ታስረዉ በነበሩበት ወቅት ብዝዎች በህክምና እርዳታ እጦት ምክንያት ህይወታቸዉን አጥተዋል ፤ለመዉለድ የተቃረቡት እናቶችም የህክምና እርዳታ አያገኙም ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል አስተዳደር የማይ ካድራ ከተማ ጊዚያዊ ከንቲባ ሆነዉ የተሸሙት አቶ ደጋለም ሲሳይ ለሮይተርስ ያሉት በድንኳን የተሰራዉና ጊዚያዊ እስር ቤት የተባለዉን ቦታ “አስተማማኝ ቤት” ወይም  “safe house” ነዉ ሁሉም አስፈላጊ የሚባሉ አቅርበቶች ያሟላ ነዉ ብለዉ ያስተባብሉ፡፡ አቶ ደጋለም ወደ 70 የሚጠጉ የትግራይ ተወላጆችና በግጭቱ ተሳትፈዋል የተባሉት ተይዘዋል ያሉ ሲሆን 700 የሚጠጉ ደግሞ ሊደርስባቸዉ ከሚችለዉ ጥቃት ፈርተዉ ተደብቀዋል ይላሉ፡፡

ፖሊስ 35 የአማራ ተወላጆችን ገድለዋል ተብለዉ ተጠርጥረዉ የተያዙት ወደ አዲስ አበባ ተዘዋዉረዉ ከእንዚህ 22ቱ ጉዳያቸዉ ለፍርድቤት የቀረበ ሲሆን የተቀሩት በነጻ ተለቀዋል ያለዉ የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ነዉ፡፡

በጥር ወር ላይ በማይ ካድራ የማቆያ ቦታዎች የነበሩ የትግራይ ተወላጆች በፖሊስ ከተከበቡ በኋላ ወደ አዉቶቢስ በሀይል ተጭነዉ ወደ ተከዘ ወንዝ መጣላቸዉ ዘገባዉ ያሳያል፡፡ የዚህ ድርጊት ሰለባ ከሆኑት መካከል አንድ ብርሀነ ሲሆኑ ከወንዙ ራሳቸዉን ጎትተዉ እንዳስወጡ ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡ በወንዙ ዳርቻ ላይ በደርዘን የሚቆጠሩ ሬሳዎች እንዳዩ ይመሰክራሉ፡፡ አብዛኞቹ ዓዲ ጎሹ ተብሎ ከሚጠራዉ አካባቢ የተወሰዱ ሲሆን ሌሎችን ግን ማወቅ እንዳልቻሉ ነዉ የሚናገሩት፡፡ ብርሀነ በሁለቱም እግሮቹ በጥይት ተመቶ ጉዳት ደርሶበታል፡፡

ቁጥራቸዉ በዉል የማይታወቁ የትግራይ ተወላጆች ተገድለዋል፡፡ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ለሮይተርስ  የማይካድራዉን ግጭት ለማጣራት ኢሰመኮ ከተባበሩት መንግስታት  ድርጅት ጋር በመሆን ያጣራል ብለዋል፡፡

በህዳር ወር ሁለተኛዉ ሳምንት ላይ የትግራይ ተወላጅ የሆኑትና ተፈናቅለዉ በሱዳን ተጥልለዉ የሚገኙት ወ/ሮ መባለ የዘጠኝ ልጆቻቸዉ አባት የሆኑትን ባለቤታቸዉ ጋር እስካሁን አልተገናኙም፡፡

ወ/ሮ መባለ የምእራብ ትግራይን አማራ አመራሮች እያስተዳደሩ ነዉ ያሉ ሲሆን አዲስ መታወቂያ እየተሰጠ መሆኑና የትምህርትና ጤና ተቋማት በአማራ ፖሊሶችና ሚሊሻዎች ቁጥጥር ስር ነዉ ይላሉ፡፡ የአማራ ቤተሰቦች በደርግ ስርአት ግዜ ትተዉት የነበሩትን መሬት ህወሓት ወስዶብን ነዉ እንጂ የኛ ነበር በማለት እስካሁን 10 ቤተሰቦች እንደተወሰዱ ይናገራሉ፡፡

የሮይተርስ ልኡክ ምእራብ ትግራይን ሲጎበኝ በየመንገዱቹ አዲስ ከትግርኛ ወደ አማርኛ የተተረጎሙ ጽህፎች ማየቱ በዘገባዉ አካትዋል፡፡ ወደ ዳንሻ በሚወስደዉ መንገድም አዲስ አቅጣጫን የሚያመለክት ታፔላ ያገኘ ሲሆን ጽሁፉም “ የአማራ መሬት” ይላል

ሙሉ ለሙሉ የወደሙ የትግራይ ገጠሮች አሉ፡፡ በአንድ ሹማሪ የተባለ ገጠራማ አካባቢ በመተዎች የሚቆጥሩ ቤቶች ወድመዋል እንዲሁም ተቃጥለዋል፤ በትግርኛ የተጻፉ የትምህርት ቤት ምጻህፍቶች ተቀዳድተዉ ተጥለዋል፡፡

የምእራብ ትግራይ የደህንነት ሀላፊ ሆነዉ የተሾሙት ኮሎኔል ደመቀ ዘዉዱ የአማራ ተወላጆች መልሶ በማይ ካድራ እንዲቋቋሙ ያስተባበራል ፡፡ እኝህ ሀላፊ በፋኖ የትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት ደርሷል የሚለዉ ፍጹም ሀሰት ነዉ ይላሉ፡፡

በአማራ ክልል አስተዳድር የተሾሙት አቶ የአብስራ በሮይተርስ ለቀረበላቸዉ እንዳልመለሱ ዘገባዉ ያመላከተ ሲሆን የትግራይ ተወላጆች በአማራ ሀይሎች ጥቃት ደረሰባቸዉ የሚለዉን ግን እንዳማይቀበሉት አሳዉቀዋል፡፡

በማይ ካድራ የመጀመሪያዎቹ ግድያዎች የትግራይ ተወላጆች በአማራዎች ላይ እንደተፈጸሙ ሪፖርቱ አመልክቷል ፡፡ ካፒቴን ካሳዬ መሓሪ በሚባል አንድ የትግራይ ሚሊሻ በሚመራ ወጣቶች የተከናወኑ መሆናቸውን አራት የአማራ ምስክሮች ተናግረዋል ፡፡ ሮይተርስ ጥያቄዎችን ለካፒቴን ካሳዬ በህወሓት በኩል ልኳል ፡፡ የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ካሳዬን  “እኔ አላውቀውም” ሲሉ ተናግረዋል ፡፡ ህወሓት በማይ ካድራ በአማራ ሰላማዊ ዜጎች ያነጣጠረዉ ጥቃት ላይ እጄ የለበትም ሲል  አስተባብሏል፡፡

የትግራይ ተወላጆች በብዛት የሚገኙበት ከተማ የአማራ ኃይሎች ብዙ ቦታ ማቀጠላቸው የትግራይ ተወላጅ የእይን ምስክሮች ተናግረዋል፡፡ የትግራይ ተወላጆች ወደ ነበርቡት እንዳይመለሱ እንኳን ምንም ነገር አላተረፉልንም ብለዋል ምስክሮቹ፡፡ ህዳር 16 እንድ የሮይተርስ ተንታኝ በአሜሪካ ሳተላይት ቦቦታው የእሳት ቃጠሎ እንደነበር ማረጋገጥ ተችለዋል ነው የተባለው፡፡

ከቤልጅየም የጋንት ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ጃን ኒሰን በማህበራዊ አውታር መረቦች እና በምስክሮች ዘገባዎች  በትግራይ ውስጥ የሰላማዊ ሰዎችን ሞት የሚከታተል ፕሮጀክት እየተቆጣጠሩ ሲሆን ተጎጂዎችን ከሚያውቁ ሰዎች ጋር መረጃውን በማጣራት መረጃ አግኝተዋል፡፡

ቡድናቸው ከ 8000 በላይ ሲቪሎች መገደላቸውን የሚገልፅ ዘገባ እንዳላቸውና ከእነዚህ 2,562 የሚሆኑትን ለይቷል ብሏል፡፡

የብሄር ግጭቱ ከትግራይ ባሻገር እጅግ እያስተጋባ ይገኛል። ይህ ጦርነት በአፍሪካ ሁለተኛ የህዝብ ብዛት ያላት ኢትዮጵያ አንድነት እጅግ አስጊ ነው፡፡ የአማራ አስተዳደር በሁለቱ ወገኖች አከራካሪ ከሆኑ ቦታዎች አንድ ሦስተኛ የሆነ የትግራይ መሬት መውሰድ ይፈልጋሉ፡፡ የአማራ ክልል መንግስት ምዕራብ ትግራይን ተቆጣጥሬዋለሁ ብሏል ፡፡ ተወካዮቹ እዚያ እስከ ግማሽ ሚሊዮን አማራዎችን ለማቋቋም አቅደዋል ፡፡

የክልሉ መንግስት ቃል አቀባይ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለሮይተርስ እንደገለጹት “ምዕራባዊ ትግራይ የሚባል ቦታ የለም ፣ ይህ አካባቢ የአማራ ክልል አካል ነው” ብለዋል

በምዕራብ ትግራይ በአማራ የተሾሙት አስተዳዳሪ ያአብስራ እሸቴ የአማራ ኃይሎች የትግራይ ተወላጆችን ገድለዋል የሚል ማንኛውም ክስ “መሬት የለሽ እና ከእውነታው የራቀ ነው” ብለዋል ፡፡

የተባበሩት መንግስታት በትግራይ ጦርነት ውስጥ በሁሉም ወገኖች ሊከሰቱ ስለሚችሉ የጦር ወንጀሎች ተናግሯል ፡፡ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንኬን በመጋቢት ወር የዘር ማጽዳት ድርጊቶች እንደነበሩ ገልፀው የአማራ ኃይሎች እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡ በሚያዝያ ወር ሮይተርስ አንድ የክልል ባለስልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ “የወሲብ ባርነት” ብለው በገለፁት ሁኔታዎች መካከል በማዕከላዊ ትግራይ ውስጥ የተፈጸሙ ስቃይ እና የተደፈሩ ሴቶች ዘገባዎችን በዝርዝር አስቀምጧል ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ለዚህ ጽሑፍ ዝርዝር ጥያቄዎች መልስ አልሰጠም ፡፡ “ዒላማ የተደረገ ፣ ሆን ተብሎ የዘር ማጽዳት” አለመካሄዱን አስተባብሏል ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መጋቢት ወር ላይ ለፓርላማው ባደረጉት ንግግር ለአማራ ኃይሎች ጥብቅና ቆመዋል ፡፡ ይህንን ኃይል እንደ ዘራፊና ድል አድራጊ አድርጎ መሳል በጣም የተሳሳተ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ፣ መንግሥት የጥቃቶች ሪፖርቶች የተጋነኑ እንደሆኑና ወንጀሎች በተፈፀሙበት ደግሞ በሕግ መሠረት እንደሚጣዩ ነው የገለጹት፡፡

አውሎ ሚድያ ሰኔ 02/ 2013 ዓ.ም 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ