“በጦርነቱ ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ ሁሉም አካላት ለሰብአዊ እርዳታ ሲሉ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ አለባቸው” – ኒክ ዳየር

0
147

ከአንድ ሳምንት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው የነበሩት የዩናይትድ ኪንግደም የረሃብ መከላከል ልዩ መልዕክተኛ ኒክ ዳየር ወደ ትግራይ ክልል አቅንተው ነበር።

ልዩ መልዕክተኛው በጦርት ውስጥ ባለችው የትግራይ ክልል የነበራቸውን ቆይታ ሲያጠቃልሉም የተመለከቱትን ሁኔታ “ቀውስ” ሲሉ ጠርተውታል።

ከጉብኝታቸው መልስ በሰጡት አስተያየትም “በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ በፍጥነት እያሽቆለቆለ ነው። የረሃብ አደጋን ለማስቀረት ያለው ብቸኛ መንገድ ጦርነቱን አሁኑኑ ጋብ ማድረግ ነው። በጦርነቱ ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ ሁሉም አካላት ለሰብአዊ እርዳታ ሲሉ ተኩስ አቁም ማድረግ አለባቸው” ሲሉ መልክት አስተላልፈዋል።

ኒክ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት በዚህ መልዕክት የግብርና ሥራዎች እንዲጀመሩ እና በተለይም ገበሬዎች ዘር መዝራት እንዲጀምሩ ግጭቱን ጋብ ማድረግ አንገብጋቢ መሆኑን አክለው ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲ የሕዝብ ግንኙነት አና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሉሲ ጎርደን በትግራይ ክልል ያንዣበው ይህ ሰው ሰራሽ የረሃብ አደጋ ሊቀለበሰ የሚችለው አስቸኳይ እርምጃዎች አሁኑኑ የሚወሰዱ እንደሆነ ብቻ ነው ይላሉ።

“የተኩስ አቁም እንደሚደረግ ተስፋ እናደርጋለን፣ የሲቪሎችን ስቃይ ለማቆስቆም ከታሰበ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች በትግራይ ሙሉ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲችሉ መደረግ አለበት” ሲሉ ተናግረዋል።

“የተኩስ አቁም ከተደረገ፣ ገበሬዎች ሰብላቸወን መዝራት ከቻሉ እና የረድኤት ተቋማት እርዳታ እንደልብ ማዳረስ ከቻሉ የረሃብ አደጋውን መቀልበስ ይቻላል” ሲሉ ነው ሉሲ የገለጹት።

ኒክ በትግራይ ካደረጉት ቅኝት በኋላም ስልታዊ የሆነ ግድያ ብሎም የሴቶች መደፈር እንዳለ ገልፀው ነበር።

ኤምባሲውም በትግራይ ክልል ካለው ሕዝብ 5.2 ሚሊዮን ወይም 90 በመቶው በረሃብ ስጋት ውስጥ መውደቁን ጠቅሶ “በትግራይ ያለው ሁኔታ እጅግ የከፋ ነው” ሲልም ገልፆታል።

የዩኬ የረሃብ መከላከል ልዩ መልዕክተኛ ኒክ ያቀረቡትን ጥሪም የተለያዩ የዓለም አገራት ለቀናት በጋራ አስተጋብተውታል።

አሜሪካ፣ አውስትራሊያ እና ካናዳ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ብሎም ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲደረግ ጥያቄ ያቀረቡ አገራት ናቸው።

ኒውዚላንድ፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ኔዘርላንድ፣ ስዊድን እና ኖርዌይ ይህንኑ ጥሪ የተቀላቀሉ የአውሮፓ አገራት ናቸው።

የዩኬ መንግሥት ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ በተደጋጋሚ የኤምባሲውን ባለሞያዎች ወደ ትግራይ በመላክ ሁኔታውን ሲከታተል መቆየቱን እና እስከአሁን 22 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።

ኤምባሲው በራሱ ከሚሰበስበው መረጃ በተጨማሪ ከታማኝ አጋሮቹ እና በእርዳታ ድርጅቶች አማካኝነት ቀውሱ ከተከሰተ ጀምሮ መረጃዎችን በመሰብሰብ የተለያዩ ሥራዎቸን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጿል።

በልዩ መልዕክተኛው በኩል ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በማስተባበር የተኩስ አቁም በማድረግ ሰብአዊ እርዳታ ማዳረስ እንዲቻል ለማድረግ እየሰራ እንደሆነ ኤምባሲው ገልጿል።

“በመተባበር ድምፃችንን እያሰማን ነው። ይህም ወደ ሚመለከታቸው አካላት ጆሮ ይደርሳል እንዲሁም ለትግራይ ሕዝብ በዚህ ወሳኝ የእርሻ ወቅት ከዚህ ጦርነት እረፍት ያገኛል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ የኤምባሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ገልፀዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድን በአካል በማግኘት ጭምር ስጋታቸውን መግለፃቸውን ሉሲ አስታውሰዋል።

አክለውም ለከፍተኛ ባለስልጣናት ስለጉዳዩ አሳሳቢነት እየገለፁ እንሆነ አክለዋል።

“ችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲበጅለት ጥሪ እናቀርባለን” ሲሉ ሉሲ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አውሎ ሚድያ ግንቦት 27 / 2013 ዓ.ም 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ