ጥምር መንግሥት መመሠረት ለእስራኤል አደጋ ነው – ኔታኒያሁ

0
75

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይዋቀራል ተብሎ የሚጠበቀው አዲስ የጥምር መንግሥት ለአገሪቱ “የደህንነት አደጋ” እንደሚሆን አስጠነቀቁ።

የአክራሪ-ብሔርተኝነት መሪ የሆኑት ናፍታሊ ቤኔት መሃል ሰፋሪ ከሚባሉት ያየር ላፒድ ጋር ድርድሩን እንደሚቀላቀሉ ከተናገሩ በኋላ ነው ኔታኒያሁ ለቀኝ ክንፍ ፖለቲከኞች ስምምነቱን እንዳይደግፉ ጥሪ ያቀረቡት።

ላፒድ አዲስ የጥምር መንግሥት ለማቋቋም እስከ ረቡዕ ድረስ ቀን ያላቸው ሲሆን ከተሳካላቸው በአገሪቱ ታሪክ ለረጅም ግዜ በጠቅላይ ሚኒስቴርነት የቆዩት የኔታኒያሁ የስልጣን ዘመን ያበቃል።

በማጭበርበር ክስ ፍርድ ቤት የቀረቡት ኔታንያሁ እ.ኤ.አ. በመጋቢት ወር በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ አብላጫ ድምፅ ማግኘት አልቻሉም ነበር። በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ አራት ግዜ አጠቃላይ ምርጫ ቢካሄድም ኔታኒያሁ አብላጫ ድምፅ ማግኘትም ሆነ የጥምር መንግሥት ለመመስረት የሚሆን ስምምነት ማድረግ ሳይችሉ ቆይተዋል።

“የግራ ዘመም የጥምር መንግሥት አትመስርቱ፣ ይህ ለእስራኤል ደህንነት አደገኛ ነው” ሲሉ የ 71 ዓመቱ ኔታኒያሁ ተናግረዋል።

ኔታኒያሁ ለ12 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆዩ መሪ ሲሆኑ፤ የአንድ ትውልድ እድሜ ላለው ግዜ የእስራኤል ፖለቲከ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይዘው ቆይተዋል።

የ49 ዓመቱ ቤኔት በበኩላቸው ፓርቲያቸው የጥምር መንግሥት ለመመስረት የሚደረገውን ድርድር እንደሚቀላቀል በቴሌቪዢን በተላለፈ መልክታቸው ላይ አስታውቀዋል።

“ኔታንያሁ ከዚህ በኋላ ቀኝ ዘመም መንግሥት ለማቋቋም አይሞክርም፣ ምክንያቱም እንደሌለ ስለሚያውቀው ነው” ያሉት ቤኔት፤ “የእስራኤል ብሔረተኛ ቡድንን እንዲሁም መላው አገሪቱን ከግሉ አቋም ጎን ለማሰለፍ እየሞከረ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ቤኔት መግለጫውን ከመስጠታቸው በፊት የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን በተዘረዘሩት የስምምነት ነጥቦች መሠረት ቤኔት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁን እንደሚተኩ እና በኋላም ለ57 ዓመቱ ለማ ላፒድ በቀጣይ ዙር ስልጣኑን እንደሚሰጧቸው ተዘግቧል። ስለ ስምምነቱ በይፋ የተባለ ነገር የለም።

ለስምምነት የቀረበው ጥመረት ከቀኝ ፣ ግራ እና ማሃል ሰፋሪ የሆኑ ፖለቲከኞችን ይሰበስባል። ፓርቲዎቹ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ብዙም የሚያመሳስላቸው ነገር ባይኖርም፣ ቤኒያሚን ኔታንያሁ የስልጣን ዘመናቸው እንዲጠናቀቅ ባላቸው ፍላጎት ላይ ግን ይስማማሉ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አውሎ ሚድያ ግንቦት 23 / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ