እነ እስክንድር ነጋ በእስር ቤት ባሉበት የምርጫ ቅስቀሳ እንዲያደርጉ ፍርድ ቤቱን ጠየቁ

0
82

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ለመጪው ሀገራዊ ምርጫ ካሉበት እስር ቤት ሆነው የተለያዩ የምርጫ ቅስቀሳ ሂደቶችን እንዲያደርጉ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ጠየቁ።

አመራሮቹ ጥያቄውን ያቀረቡት በትላንትናው ዕለት የሰበር ሰሚ ችሎት በመጪው ምርጫ በዕጩነት ተመዝግበው መወዳደር እንደሚችሉ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ነው። 

አራቱን የባልደራስ ፓርቲ አመራሮችን ወክለው ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ያቀረቡት አቶ ስንታየሁ ቸኮል፤ ከእስር ቤት ሆነው መግለጫዎች እንዲሰጡ እና የተለያዩ የቅስቀሳ ወረቀቶችን እንዲበትኑ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

አቶ ስንታየሁ ጥያቄውን ያቀረቡት እርሳቸውን ጨምሮ የአምስት ተከሳሾችን መደበኛ የክርክር ሂደትን ለመመልከት ለተሰየመው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ-ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ነው።

ችሎቱ ዛሬ ቀጠሮ ይዞ የነበረው በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የተቆጠሩ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን የአሰማም ሂደት በሚመለከት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ተመልክቶ ሂደቱን ለመወሰን ነበር።

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ግንቦት 4 በነበረው ችሎት፤ ዐቃቤ ህግ በምስክሮቹ ላይ ይደርሳል የሚላቸውን ተጨባጭ የደህንነት ስጋቶች ለከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ጉዳዩ ክርክር እንዲደረግበት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

የከፍተኛው ፍርድ ቤት በዛሬው ውሎው፤ ዐቃቤ ህግ የደህንነት ስጋቶች የሚላቸውን በሬጅስትራር በኩል ሐሙስ ግንቦት 19 ቀን እንዲያቀርብ አዝዟል። ዐቃቤ ህግ ለፍርድ ቤቱ የሚያስገባው ማመልከቻ የሚሰጣቸው የተከሳሽ ጠበቆች፤ መልሳቸውን ለሰኞ ግንቦት 23 አዘጋጅተው ለችሎት እንዲያቀርቡም ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ቀጠሮ በመሰጠቱ ቅር የተሰኙት የተከሳሽ ጠበቆች፤ በቀላል ነገሮች ቀጠሮ እየበዛ ተከሳሾች እየተጉላሉ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

“ስንጠብቅ የነበረው ክርክር እናደርጋለን ብለን ነበር” ሲሉም ተደምጠዋል። ነገር ግን ፍርድ ቤት ሁለቱም ወገኖች በትዕግስት እንዲጠብቁ ጠይቆ ጉዳዩን በአጭር ጊዜ እንደሚቋጨው ለጠበቆች ቃል ገብቷል። 

በዛሬው የችሎት ውሎ ላይ አራቱም የባልደራስ ተከሳሽ አመራሮች በአካል ተገኝተዋል። አመራሮቹን ወክለው የተናገሩት አቶ ስንታየሁ ቸኮል፤ ፍርድ ቤቱ ይሄን ሁሉ ጊዜ እነሱን ለማዳመጥ ለሚያደርገው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

“እንደዚህ አይነት ባህል ሊለመድ ይገባል” ሲሉም የችሎቱን አካሄድ አሞካሽተዋል። አቶ ስንታየሁ በዚሁ ንግግራቸው ለመጪው ሀገራዊ ምርጫ በዕጩነት ተመዝግበው መወዳደር እንደሚችሉ በፍርድ ቤት እንደተፈቀደላቸው ጠቅሰው፤ ከእስር ቤት ሆነው “ከውስጥ ወደ ውጭ” በተወካዮቻቸው በኩል የምርጫ ቅስቀሳዎችን እንዲያደርጉ ችሎቱን ጠይቀዋል። 

“ለብዙ ጊዜ የተገፋውን የአዲስ አበባ ህዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ በመረጠው እንዲተዳደር የበኩላችሁን እንድትወጡ እጠይቃለሁ” ለሚለው የአቶ ስንታየሁ ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ምንም አይነት ምላሽም ሆነ አስተያየት ሳይሰጥ የዛሬው ችሎት ተጠናቅቋል።

በዛሬው ችሎት ላይ በርከት ያሉ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ደጋፊዎች ተገኝተው ሂደቱን ተከታትለዋል ሲል ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡

አውሎ ሚድያ ግንቦት 17 / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ