በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የጸጥታ ኃላፊን ጨምሮ 7 ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ

0
79

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ውስጥ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት አንድ የአካባቢው ባለሥልጣንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸው ተነገረ፡፡

በምዕራብ ጉጂ ዞን ውስጥ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት በዞኑ የሚገኘው ገላና ወረዳ የጸጥታና የደኅንነት ኃላፊ የሆኑትን አቶ ጃርሶ በካሎን ጨምሮ ሰባት ሰዎች በታጣቂዎቹ መገደላቸውን የወረዳው የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ገበየሁ ያደቴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ገበየሁ እንዳሉት ጥቃቱ የተፈጸመው ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 14/2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ 11 ሰዓት አካባቢ ሲሆን በአጠቃላይ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል።

ከደቡብ ክልል የአማሮ ወረዳ ጋር በሚዋሰነው በዚህ አካባቢ እንዲህ ያለው ጥቃት ሲፈጸም የመጀመሪያ አይደለም። ከዚህ በፊትም በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ግድያዎች መፈጸማቸው ይታወሳል።

ባለፈው መጋቢት ወር ሁለቱ ወረዳዎች በሚያዋሰኑበት ሥፍራ ስብሰባ ላይ በነበሩ አመራሮችና ነዋሪዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሰባት ሰዎች ሲገደሉ ስድስት ደግሞ ቆስለው ነበር።

በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ገበየሁ ያደቴ  እንደተናገሩት ጥቃቱ በታጣቂዎቹ የተፈጸመው ኃላፊውና ሌሎች የጸጥታ አካላት ለሥራ እየተጓዙ በነበረበት ጊዜ ነው።

“በዚህም በወረዳው የጸጥታና የደኅንነት ኃላፊ አቶ ጃርሶ በካሎ የተመራ ቡድን የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ቦሬ ቀበሌ እየተጓዘ ሳላ ጨልቤሳ ሾሮ በተባለ ሥፍራ ላይ ነው ጥቃቱ የተፈጸመባቸው” ብለዋል።

በጥቃቱም ከወረዳው አስተዳደር ወገን የነበሩ ሰባት ሰዎች ሲገደሉ ከታጣቂዎቹ በኩል ደግሞ ሁለት ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

በጥቃቱ ሁለት የሚሊሻ አባላት፣ ሦስት የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አባላት፣ የወረዳው ጸጥታና ደኅንነት ኃላፊና እና የጽህፈት ቤቱ የደኅንነት ባለሙያ በአጠቃላይ 7 ሰዎች ተገድለዋል።

በታጣቂዎቹ ከተገደሉት በተጨማሪ ይጓዙበት የነበረው ተሽከርካሪ ሾፌር እና ሌሎች 7 ሰዎች ደግሞ በተለያየ ደረጃ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ዲላ ሆስፒታል ተወስደው የህክምና እርዳታ እያገኙ መሆኑን አቶ ገበየሁ ገልጸዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባወጣው መረጃ በዚህ ዓመት ብቻ በኦሮሚያ ክልል ‘ሸኔ’ በተባለው ታጣቂ ቡድን በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ18 በላይ በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ 112 የፖሊስ አባላት እንዲሁም 57 በሚሊሻ አባላት በምዕራብና በደቡብ ኦሮሚያ ውስጥ ተገድለዋል።

አውሎ ሚድያ ግንቦት 16 / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ