መንግስት በትግራይ ጦርነት ላይ የኬሚካል መሳርያ ተጠቅመዋል – ዘ ቴሌግራፍ

0
40

ትላንትና ቴሌግራፍ የተባለውና መቀመጫው ለንደን ያደረገው ጋዜጣ አሁን በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል እየተካሄደ  ባለው ጦርነት የኬሚካል መሳርያ ተጠቅመዋል ሲል በድረገጹ አስነብቧል፡፡

እንደጋዜጣው ሪፖርት ከሆነ ‘ዋይት ፎስፈረስ’ ከሚባው የኬሚካል ጦር መሳርያ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ኬሚካል እንደሆነና በንጹሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ የቃጠሎ አደጋ መድረሱም ገልጸዋል፡፡

ቴሌግራፍ በዘገባው በትግራይ ክልል በኬሚካሉ ቃጠሎ የደረሰባቸው ንጹሀን ዜጎች እንዳሉ ገልጾ ይህም የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል በስፋት አትቷል፡፡

ከትግራይ አገኝኃቸው ባላቸው ምስክሮች፤ ተጎጂዎች እንዲሁም በኬሚካሉ ምክንያት ሰዉነታቸው የተቃጠሉ ዜጎች በጋዜጣው አስፍረዋል። ይህም የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦር በሲቪል ማህበረሰቦች አከባቢ በከፍተኛ ሁኔታ የሚነድ መሳሪያ ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል ሲል ገልጿል።

አናገርኳቸው ያላቸው የኬሚካል የጦር መሣሪያ ባለሞያዎች ከትግራይ ተቀረፀው የወጡትን ምስሎች በዓለም አቀፍ ሕግ በሰው ዒላማዎች ላይ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ከሚከለከለው ከ ‘ዋይት ፎስፈረስ’ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው ስለማለታቸው አስነብቧል።

ከተጎጂዎቹ መካከል በማዕከላዊ ትግራይ የ ‘ዓዲ አይቆሮ’ መንደር ነዋሪ የሆነች የ13 ዓመት ታዳጊ ቅሳነት ገብረሚካኤል የምትገኝበት ሲሆን ሚያዚያ 20 መኖሪያ ቤታቸው ጥቃት ሲሰነዘርበት ከፍተኛ ቃጠሎ ደርሶባታል ብሏል።

ታዳጊዋን በስልክ እንዳነጋገሯትና ቃጠሎው ከደረሰባት በኋላ ወደ ሆስፒታል ሄዳ የተነሳችው ፎቶ የእጇ፣ የእግሯ እና የፊቷ ቆዳ መቃጠሉን እንደሚያሳይ ዘገባው ይገልጻል።

ሌላኛው ተጎጂ፥በምስራቅ ትግራይ ዓዲ ዎልዎ መንደር ነዋሪ የሆነው የ18 ዓመት ወጣት የማነ ወልደሚካኤልም በተመሳሳይ ከፍተኛ ቃጠሎ ደርሶበታል።

ዋይት ፎስፈረስ ኬሚካል ማለት በአየር ሲበተን በቦታው አክስጅን እንዲያጠፋ የሚደርግና የሰዎች ቆዳ ሲያገኝ የሚቃጥልና ለማጥፋትም ከባድ ነው፤ ይህንንም አይነት ኬሚካልም በቬትናም ጦርነት ጥቅም ላይ እንደዋለው ከነፓልም መርዛማ ኬሚካል ጋር ተመሳሳይነት እንዳለዉ ይነገርለታል ፡፡

ይህንን አይነት ኬሚካል በሌሊት የጦር ሜዳውን ለማብራት ወይም ታክቲካዊ የጭስ ማሳያዎችን ለማቅረብ በሕጋዊ መንገድ ሊያገለግል ይችላል ፡፡

የቴሌግራፍ ዘገባ በበኩሉ የተባበሩት መንግሥታት የጄኔቫ ስምምነትን አጣቅሶ፤ ንጹሀን ዜጎች ላይ ኬሚካል የጦር መሣሪያ መጠቀም ዓለም አቀፍ መርህን እንደሚጥስ ይጠቅሳል።

“እነዚህ አሰቃቂ ጉዳቶች በሰሜን ምስራቅ እና በሰሜን-ምዕራብ ሶሪያ በደረሱ ጉዳቶች ላይ ካየሁት ጉዳቶች ጋር በጣም ተመሳሳይነት አላቸው ሲሉ በእንግሊዝ የጋራ ኬሚካል ፣ ባዮሎጂካል ፣ ራዲዮሎጂ እና ኑክሌር ክፍለ ጦር አዛዥ የነበሩት ሀሚሽ ዴ ብሬትቶን-ጎርደን ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ጉዳዩን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ በቴሌግራፍ ዘገባ ላይ በትግራይ ክልል ንጹሀን ዜጎች በኬሚካል ተቃጥለዋል የሚለውን ዘገባ አስተባብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መግለጫ ከዘገባው በተቃራኒው “ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የኬሚካል መሣሪያዎች ድንጋጌ ስለምታከብር ክልከላ የተጣለባቸውን የጦር መሣሪያዎችን አልተጠቀመችም። አትጠቀምም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ለዚህ ዘገባ ባወጣው መግለጫ ላይ “እንዲህ ያሉ የተሳሳቱና ኃላፊነት የጎደላቸው ዘገባዎች ውጥረት ከማባባስ ያለፈ ሚና እንደሌላቸው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሳውቀናል” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ዘገባው በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር እየተረገ ያለው ጥረት አንድ አካል እንደሆነ የሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ መግለጫ ጠቅሷል።

የቴሌግራፍ ዘገባ እንደሚለው፤ ንጹሀን ዜጎች በነጭ ፎስፈረስ ቃጠሎ እንደደረሰባቸው የሚጠቁም መረጃ ማግኘቱን አመልክቷል።

አውሎ ሚድያ ግንቦት 16 / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ