የኤርትራ ወታደሮች በአክሱም 110 ንጹሃን ሰዎች ገድለዋል – ጠቅላይ አቃቤ ህግ

0
67

በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ህዳር 19 እና 20፣ 2013 ዓ.ም በነበረው ውጊያ የኤርትራ ወታደሮች 110 ንጹሃን ሰዎች መግደላቸውን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባውጣው የምርመራ ሪፖርት አስታወቋል፡፡

አቃቤ ህግ በአስገድዶ መድፈርና በንጹሃን ግድያ ተሳትፈዋል ያላቸውን 53 የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይም ክስ መስርቷል::

አቃቤ ህግ በትናትናው እለት በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለውን ምርመራ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫው በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ህዳር 2013 ዓ.ም ተፈጽመዋል የተባሉ ወንጀሎች ላይ የምርመር ስራ መቀጠሉን አስታውቋል።

እስካሁን ባደረገው ምርመራም አክሱም ከተማ ህዳር 19 እና 20፣ 2013 ዓ.ም በነበረው ውጊያ 110 ንጹሃን ሰዎች በኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን አረጋግጧል።

በምርመራው መሰረትም 70 ሰዎች በአክሱም ከተማ ውስጥ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ መንገድ ላይ እያሉ መገደላቸውን ያመላከተው ምረመራው፤ ከሟቾቹ ውስጥም ወታደራዊ የደንብ ልብስ ባይለብሱም በጦርነቱ የተሳተፉ ሰዎች መኖራቸው መረጋገጡን አስታውቋል።

በሌላ መልኩ 40 ንጹሃን ሰዎች ደግሞ የኤርትራ ወታደሮች ቤት ለቤት ባደረጉት አሰሰሳ ከቤታቸው እንዲወጡ ተደርገው እና በቤታቸው ውስጥ መገደላቸውንም ምርመራው አመላክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም በከተማዋ በርከት ያሉ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት መድረሱን ያመላከተው ጠቅላይ አቀቤ ህግ ሪፖርት፤ ከእነዚህም ውስጥ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ካምፓሶች፣ ቅድስት ማርያም ሆስፒታል ብራና ሆቴል ይገኙበታልም ብሏል።

በወቅቱ በአክሱም በነበረው ውጊያ የደረሰውን ጉዳት ለማጣራት 119 ሰዎች የምስክርነት ቃል እንዲሰጡ መደረጉን፣ የህክምና ማስረጃዎች፣ የፎቶ እና ቪዲዮ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡንም ጠቅላይ አቃቤ ህግ በሪፖርቱ ገልጿል፡፡

ጠቅላይ አቃቤ ህግ የወታደራዊ ግዴታ በሌለበት ወቅት በግድያ የተጠረጠሩ 28 የኢትዮጵያ ወታሮች ላይ ክስ መመስረቱን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ጾታ ጥቃትና አስገድዶ መድፈር የፈጸሙ 25 ወታደሮችም ክስ ተመስርቶባቸዋል ብሏል አቃቤ ህግ፡፡ በክሶቹ ላይ በአጭር ጊዜ ፍድድ እንደሚሰጥ አቃቤ ህግ ገልጿል፡፡

በተመድ የኤርትራ አምበሳደር ሶፊያ ተስፋማርያም በሚያዚያ ወር መጨረሻ ለተመድ በጻፊት ደብዳቤ የኤርትራ ጦር በትግራይ ግጭት መሳተፉን አምነው፤ጦሩ በአስገድዶ መድረርና ጾታ ጥቃት ተሳትፏል የሚለውን የተመድ ሪፖርት ሀሰት ነው ሲሉ አስተባብለው ነበር፡፡

አምባሳደሯ “አንዣቦ የነበረው ስጋት በአብዛኛው በመወገዱ ኤርትራና ኢትዮጵያ የኤርትራ ኃይሎችን ለማስወጣትና የኢትዮጵያ ሠራዊት በድንበር ላይ እንዲሰማራ ለማድረግ በከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው አማካይነት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል” ብለው መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ቀደም ብሎው ወደ ኤርትራ አቅንተው በነበረበት ወቅት ኤርትራ ጦር ለማስወጣት መስማማታቸውን አስታውቀው ነበር፡፡

በክልሉ ግጭቱን ተከትሎ የንጹሃን ግድያና ፆታዊ ጥቃት ጨምሮ የሰብአዊ መብት ጥሰት በግጭቱ ተሳታፊ ሃይሎች መፈጸማቻን በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ)ና በተለያዩ የአለምአቀፍ የመብት ድርጅቶች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በግጭቱ ሳቢያ ከሁለት ሚሊዮን ሰዎች በላይ ለመፈናቀል የተዳረጉ ሲሆን፤ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው መጥቀሱ ይታወሳል፡፡

አውሎ ሚድያ ግንቦት 14 / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ