በምዕራብ ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ በትናንትናው ዕለት በተካሄደ ሰልፍ በሰውና በንብረት ጉዳት መድረሱ ተገለጸ

0
35

በምዕራብ ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ በትናንትናው ዕለት ሐሙስ ግንቦት 12/2013 ዓ.ም በተካሄደ ሰልፍ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ።

የብልጽግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች በቅርቡ ለሚደረገው ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ በስፍራው ሰልፍ እንደነበረ ቢቢሲ በደረገፁ አስነብቧል፡፡

በሰልፉ ላይ የህይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት እንደደረሰ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

“ድምፃቸውን በሰላማዊ መንገድ ባሰሙ ተማሪዎች ላይ የጸጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት ደርሷል” በማለት አስፍሯል።

አብን ዛሬው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ በተማሪዎቹ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በጥብቅ አወግዛለሁ ብሏል።

በተጨማሪም ለጥቃቱ ትዕዛዝ የሰጡና የፈፀሙ አካላት ላይም መንግሥት አስቸኳይ ምርመራ እንዲያደርግና ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ እንዲሁም ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግም ጠይቋል።

ፓርቲው አክሎም “ገዥው የብልጽግና መንግሥት ሕዝቡ የሚሰጠውን ፖለቲካዊ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ተቃውሞንም በአግባቡ ለማዳመጥ መዘጋጀት አለበት” ብሏል።

የመርዓዊ ከተማ ኮምዩኒኬሽን ስለጉዳዩ የሰሜን ሜጫ ወረዳ ሰላምና ደኅንነት ጽህፈት ቤትን ጠቅሶ እንዳለው ፖሊስ በንጹሃን ዜጎች ላይ ተኩሶ ገድሏል እየተባለ በሚዲያ የሚናፈሰው ወሬ ፍጹም ሐሰት ነው ብሏል።

የሰሜን ሜጫ ወረዳ ሰላምና ደኅንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ተስፋ፤ “በብልጽግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ሰልፉ በሰላም እንዳይጠናቀቅ ፍላጎት ያላቸው አካላት ሁከት ለመፍጠር ሙከራ አድርገዋል” ብለዋል።

የመርዓዊ ከተማ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊውን ዋቢ አድርጎ እንዳሰፈረው “ሰልፉን ለማደናቀፍ የተጠቀሙባቸው ምንም የማያውቁ የአገር ተረካቢ ተማሪዎችን ነው” ብሏል።

ኃላፊው ሰልፉን ለማደናቀፍ ተማሪዎችን በሽፋንነት ተጠቅመዋል ያሏቸውን አካላት አልጠቀሱም። ነገር ግን “የችግሩ ፈጣሪዎች አላማ በተለያየ ወንጀል ተጠርጥረው ፖሊስ ጣቢያ ማረፊያ ቤት ያሉ ሰዎችን የማስለቀቅ ነበር” ሲሉ ገልፀዋል።

አቶ ተመስገን ፖሊስ “ሰላማዊ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል” ያሉ ሲሆን በዚህም የድብደባ እና የአካል ማጉደል ደርሶባቸዋል ብለዋል።

በፖሊስ ደረሰ ስለተባለውም ጉዳት ሲያስረዱ አንድ የፖሊስ አባል ላይ የአካል ድብደባ ሲደርስ የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ሽጉጥ ተወስዷል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሰልፉን ለመደገፍ የመጡ አርሶ አደሮች ላይ ደብደባ ማጋጠሙንና በንብረት ላይ ጉዳትና ዘረፋ መፈጸሙን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት የችግሩን ፈጣሪዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል ፖሊስ እየሰራ ነው ያሉ ሲሆን ምርመራው ከተጠናቀቀ በኋላ መረጃው እንደሚሰጥም ኃላፊው ተናግረዋል።

አውሎ ሚድያ ግንቦት 13 / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ