በቤንሻንጉል ጉሙዝ መንግሰት እና በጉሙዝ ታጣቂ ቡድን መካከል መግባቢያ ሰነድ ተፈረመ

0
75

በመተከል ዞን እየተከሰተ ያለውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት መፍትሄ ለመስጠት በክልሉ መንግስትና በታጣቂ ቡድኑ መካከል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ ሲል የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

የቀጠናውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ በታጣቂ ቡድኑ በኩል የሚነሱ እና የጋራ በሚያደርጉ ጉዳዮች ዙሪያ የስምምነት ሰነድ በማዘጋጀት በግልገል በለስ ከተማ በትላንትናው ዕለት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ የተካሄደው በታጣቂ ቡድኑ በኩል የሚነሱ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ ለመስጠት የተሃድሶ ስልጠና እየወሰዱ ከሚገኙ አባላት ጋር ነው።

በስምምነት ሰነዱ ውስጥ ከተካተቱ ዋና ዋና አጀንዳዎች መካከል፤ ከእነዚህ ሃይሎች አቅምና የትምህር ደረጃውን በማየት በክልል ደረጃ 2 ፣በዞን ደረጃ 3 እና በወረዳ ደረጃ ደግሞ 4 የሃላፊነት ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ ፣የከተማ የቤት መስሪያ ቦታ፣ የገጠር የእርሻ መሬት እያዲያገኙ ማድረግ፣ሴቶችን አካታች ያደረገ በተለያዩ ማህበራት እንዲደራጁ ማስቻል፣በተማሩበት የሙያ መስክ እንዲመደቡ ማድረግ፣ ከአሁን በፊት ልምድ ያላቸውን ሰዎች በክልሉ ውስጥ ባሉ የጸጥታ መዋቅሮች መመደብ እና የብድር አገልግሎት መስጠት የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው።

የስምምነት ሰነዱ በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር በአቶ አሻድሊ ሃሰን እና በታጣቂ ቡድኑ ተወካይ በአቶ ጀግናማው ማንግዋ በኩል ተካሂዷል።

በስምምነት ፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ አሻድሊ ሃሰን ሰነዱ በክልሉ መንግስት በኩል ያለምንም መጓተት ተፈጻሚ እንደሚሆን ገልጸው ለዚህም ስኬት ያመች ዘንድ ስራውን ለመከታተል ከታጣቂ ቡድኑ ሶስት አባላትን ያካተተ ጊዜያዊ ጽህፈት ቤት በግልገል በለስ ከተማ መቋቋሙን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት አቅም በፈቀደና ህግና ስርዓቱን በሚፈቀደው መሰረት ሁሉም እንደሚተገበር የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ አሁን በሰላም የገቡት የታጣቂ ቡድኑ አባላት የሰላም አምባሳደር መሆናቸውን በመገንዘብ ሌሎች ወደ ሰላም ያልመጡ የታጣቂ ቡድን አባላትን ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ ጥረት እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ እና የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ ብርጋዲየር ጄነራል አለማየሁ ወልዴን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ እና የዞን አመራሮች እንዲሁም የታጣቂ ቡድኑ አባላት ተካተዋል።

አውሎ ሚድያ ግንቦት 11 / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ