በእስራኤልና ፍልስጤም መካከል በሚደረገው ውይይት አሜሪካ ትሳተፋለች

0
127

በእስራኤልና ፍልስጥኤም መካከል ያለው ግጭት ከፍ ወዳለ ጦርነት ሊያመራ ይችላል በተባለበት ወቅት ግጭቶቹን ለማርገብ ለሚደረገው ውይይት አሜሪካ ልዑኳን ልካለች።

ሃዲ አሚር ከእስራኤል፣ ከፍልስጥኤምና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከተውጣጡ ኃላፊዎች ጋር በሚደረገው ውይይት ይሳተፋሉ።

ውይይቱም የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ተስፋ ተጥሎበታል።

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በእስራኤልና በፍልስጥኤም ግጭት ላይ በነገው እለት የሚወያይ እንደሆነም ተጠቅሷል።

በእስራኤል የሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ እንዳስታወቀው የልዑኩ ጉዞ “ዘለቄታዊ ሰላም እንዲመጣ የሚሰሩ ስራዎችን ለማገዝ” እንደሆነ ቢያትትም የእስራኤልና የፍልስጥኤም ባለስልጣናት ተኩስ እንዲያቆሙ የቀረበላቸው ተማፅኖ ፍሬ አላፈራም።

ዛሬ በጥዋት እስራኤል በጋዛ ላይ የአየር ጥቃት የፈፀመች ሲሆን ፍልስጥኤማውያንም በምላሹ ሮኬቶችን አስወንጭፈዋል።

በባለፉት አምስት ቀናት በግጭት እየተናጠ ያለው ይህ ግዛት በባለፉት አመታት በቀጠናው ከተከሰተው የከፋ ነው ተብሏል።

በምስራቅ ኢየሩሳሌም በእስራኤልና በፍልስጥኤማውያን መካከል ለሳምንታት የዘለቀው ውጥረት ወደ ግጭት ያመራው በያዝነው ሳምነት መጀመሪያ ሰኞ እለት ነው።

በእስልምናና በአይሁድ እምነት ተከታዮች ዘንድ ቅድስት ተብላ የምትጠራው ስፍራ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ መጋጋል ተፈጥሮ ነበር።

ጋዛን የሚያስተዳድረው ታጣቂው ሃማስ እስራኤል ከቅድስቲቷ ስፍራ ለቃ እንድትወጣ ካስጠነቀቀ በኋላ ሮኬቶ ማስወንጨፉ ተገልጿል። እስራኤልም በምላሹ የአየር ጥቃቶችን ፈፅማለች።

ግጭቱ ከተጀመረባት እለት ጀምሮ በጋዛ እስካሁን ድረስ 133 ሰዎች እንዲሁም በእስራኤል ስምንት ሰዎች ተገድለዋል።

የፍልስጥኤም የጤና ሚኒስቴር ባለስልጣናት እንዳሳወቁት በዛሬው ዕለት ጥዋት እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት ሴቶችና ህፃናትን ጨምሮ ቢያንስ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል።

ጥቃቱ የደረሰው በምዕራባዊቷ ጋዛ ከተማ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ማዕከል ውስጥ ነው።

የሃማስ ታጣቂዎች በምላሹ ሮኬቶችን ወደ እስራኤሏ ከተማ ቤርሼባ አስወንጭፈዋል።

በትናንትናው ዕለት ግጭቶች ወደ ዌስት ባንክ ተዛምተው አስር ፍልስጥኤማውያን ሲገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጎድተዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አውሎ ሚድያ ግንቦት 07 / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ