የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መግለጫ በአክሱም የተካሄደውን ጭፍጨፋ ለመሸፋፈን ያለመ ነው – አምነስቲ ኢንትርናሽናል

0
220

የሰሞኑን የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መግለጫ በአክሱም የተካሄደውን ጭፍጨፋ ለመሸፋፈን ያለመ እንደሆነ አምነስቲ ኢንትርናሽናል ገለፀ፡፡

አምነስቲ ባወጣው መግለጫ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ በሁለት ጉዳዮች ላይ ልዩነት እንዳለው አስታውቋል፡፡

እንደ ዓለም አቀፉ ተቋም ገለጻ ከሆነ በአክሱም ተፈጸመ በተባለው ወንጀል በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከቀናት በፊት ለመገናኛ ብዙሀን በሰጠው መግለጫ በአክሱም በነበረው ውጊያ 93 ሰዎች መሞታቸውንና “ሟቾቹ ወታደራዊ የደንብ ልብስ ባይለብሱም አብዛኞቹ በጦርነቱ የተሳተፉ መሆናቸውን በምርመራው መረጋገጡን” አስታውቋል፡፡

በምርመራው “በጦርነቱ ተሳትፎ ያልነበራቸው በመንገድ ላይ የነበሩ ንጹሀን” ጭምር መግደላቸውንም ነው ዐቃቤ ህግ ያስታወቀው፡፡

“የለም ጥቃቱ ያነጣጠረው በታጣቂዎች ላይ ሳይሆን ንፁሀን ላይ ነው” ያለው አምነስቲ ኢንትርናሽናል ግን የዐቃቤ ህግን መግለጫ ተቃውሟል፡፡

“ከሞት ለማምለጥ ሲሞክሩ የነበሩ ያልታጠቁ ንፁሀን መጠቃታቸውን በምርመራ አረጋግጫለሁኝ”ም ነው አምነስቲ ያለው፡፡

በኤርትራ ሰራዊት ሲደረግ በነበረው የቤት ለቤት አሰሳ ወጣቶችና አዛውንቶችን ጨምሮ በርካታ ንጹሀን ተገድለዋል ያለው አምነስቲ እስከ አመሻሽ በቆየው የቤት ለቤት አሰሳ “በርካቶች ቤተሰቦቻቸው ፊት ተረሽነዋል” ሲል አክሏል፡፡

ወንጀሉን በመፈጸም ረገድ የኤርትራ ሰራዊት ሚናን በተመለከተም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በልኩ አላስቀመጠም ሲልም ተችቷል፡፡

የህወሓት ታጣቂዎች በኤርትራ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈፀማቸው እንዲሁም በእስር ለነበሩ ወንጀለኞች የኤርትራ ወታደራዊ የደምብ ልብስ በመስጠት ከእስር ቤት መልቀቃቸው በአክሱም ለተፈፀመ ድርጊት ምክንያት እንደሆነ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መግለፁ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጅ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከምስክሮች በቃለ መጠይቅ አረጋገጥኩት እንዳለው ከሆነ “የቤት ለቤት አሰሳ ሲያካሂዱ የነበሩት የኤርትራ ወታደሮች ከለበሱት የደምብ ልብስ በተጨማሪ በባህል እና የቋንቋ ዘያቸው ይለያሉ” ብሏል ሲል አል ዐይን ዘግቧል፡፡

በመግለጫው ማጠቃለያም “በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ጭፍጨፋ የመመርመር ኃላፊነት” እንዳለበት አስቀምጧል፡፡

አምነስቲ ምንም እንኳን መሰል ምርመራዎች በአለም አቀፍ አሰራር ፈጣን፣ የተሟሉ፣ ውጤታማ፣ ገለልተኛ እና ግልጽነት ያላቸው መሆን ቢጠበቅባቸውም፤ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያደረገውን ምርመራ በመርህ ደረጃ እንደሚቀበል አስታውቋል፡፡

ሆኖም ከመርሆቹ በመነሳት በተለይም የምርመራው ነፃነት እና ገለልተኛነት እንደሚያሳስበውና የምርመራ ግኝቶቹ ተዓማኒ እንዳይደሉም ገልጿል፡፡

በመሆኑም የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መግለጫ የኤርትራ ወታደሮች የነበራቸውን ሚና በመቀነስ ጭፍጨፋውን ለመሸፋፈን ያለመ ነው ብሏል አምነስቲ፡፡

አምነስቲ ለወደፊት ሊከሰሱ በሚችሉ አካላት ላይ ማስረጃዎች የመሰብሰብ ስልጣን ባላቸው ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ወይም አህጉራዊ ተቋማት ምርመራ እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አውሎ ሚድያ ግንቦት 06 / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ