የአለም መሪዎች ለትግራይ ድምፃቸው የበለጠ ማሰማት አለባቸው – አምንስቲ ኢንተርናሽናል

0
521

የአፍሪካና የተቀረው ዓለም መሪዎች በትግራይ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ድምፃቸውን የበለጠ እንዲያሰሙ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ድርጅት ጥሪ አቀረበ።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተሟጋች ቡድን ባወጣው መግለጫ ለስድስት ወራት በዘለቀው የትግራይ ጦርነት በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተካሂደዋል ብሏል።

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ መቶ ሺዎች ክልል ውስጥ ተፈናቅለዋል፤ እንዲሁም 63 ሺህ ሰዎች ወደ ሱዳን ተሰድደዋል ብሏል ድርጅቱ።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሌሎች ተቋማት እስከ የጦር እና ሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀልን ጨምሮ የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈፅመዋል ይላል የድርጅቱ መግለጫ።

መግለጫው አክሎም የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች በጋራ መድፈርን ጨምሮ ታዳጊና አዋቂ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት እንደፈፀሙ ማስረጃዎች አሉ ይላል።

“ስድስት ወራት ባስቆጠረው የትግራይ ግጭት የሰብዓዊ መብትና የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግጋት ጥሰቶች እንዳሉ የሚያሳዩ ማስረጃዎች እጥረት ባይኖርም ከአፍሪካ ሕብረትና ከተባበሩት መንግሥታት በቂ ምላሽ አልተሰጠም” ይላሉ የአምነስቲ የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ኃላፊ ዴፕሮስ ሙቼና።

“የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ከወራት በኋላ በትግራይ ያለው ሁኔታ እንዳሳሰበው ገልጿል። የአፍሪካ ሕብረትና የቀጣናው ሃገራት ግን በተነፃፃሪ ዝምታን መርጠዋል” ይላሉ ኃላፊው።

አምነስቲ፤ ‘ኦፕን ሶርስ’ የተሰኘ የምርመራ መንገድ እንዲሁም የሳተላይት ምስሎች ትንተና እና የቪድዮ ምስሎች ማስረጃዎችን በመጠቀም የተለያዩ ጥሰቶችን እንደመዘገበ በመግለጫው አሳውቋል።

አልፎም ድርጅቱ ከጥቃት የተረፉ ሰዎችን እንዲሁም በምስራቅ ሱዳን ያሉ ስደተኞችን በቴሌፎንና በአካል በማናገር መረጃ እንደሰበሰበ በመግለጫው አትቷል።

አምነስቲ መዝቤያቸዋለሁ ካላቸው ጥሰቶች መካከል በማይ ካድራ ከሕወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ ኃይሎች የተፈፀመው ጅምላ ግድያ እንደሚገኝበት አሳውቋል። ይህን ተከትሎ የትግራይ ተወላጅ በሆኑ የማይ ካድራ ነዋሪዎች ላይ የአፀፋ ጥቃት፣ ሕግን ከለላ ያደረገ ግድያ፣ ዘረፋና ጅምላ እሥር እንደተፈፀመ መመዝገቡን ይገልፃል።

አምነስቲ አክሎ በአክሱም ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውንና ይህም ሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ተደርጎ ሊቆጠር እንደሚችል እንዲሁም በአድዋ ከተማ ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በተፈፀመ ጥቃት ሰዎች መገደላቸውን በመግለጫው አትቷል።

አምነስቲ ከሲኤንኤን ጋር ተባብሬ አረጋገጥኩት ባለው ወንጀል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በማሕበረ ደጎ ከተማ ሕግን ከለላ አድርገው በፈረንጆቹ ጥር 15/2021 ግድያ ፈፅመዋል ብሏል በመግለጫው።

ወደ ትግራይ እንዲገቡ በየካቲት ወር ፈቃድ የተሰጣቸው መገናኛ ብዙሃን በአምነስቲና ሌሎች ድርጅቶች ተፈፅመዋል ተብለው የተጠቀሱትን ጥሰቶች እንዳረጋገጡና አስከፊ ጥሰቶችን እንዳጋለጡ ድርጅቱ ይገልፃል።

ከእነዚህ መካከል በምዕራብ ትግራይ የመንግሥት ደጋፊዎች በሚባሉት የአማራ ልዩ ኃይልና ፋኖ እንዲሁም የአማራ ሚሊሻ የተፈፀመው የዘር ማፅዳት ይገኝበታል ይላል አምነስቲ።

በዚህ የዘር ማፅዳት ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋልም ይላል። አምነስቲ ይህን በምዕራብ ትግራይ ተፈፀመ የተባለውን ጥሰት በግሉ ማጣራት ባይችልም ሁኔታውን ማጣራት እንደሚቀጥልበት አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ በጣም አስከፊ የሆኑ ሰፊ የመድፈር ወንጀሎች እንዲሁም ሌሎች በጋራ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ሕፃናትና አዋቂ ሴቶች ላይ እንደተፈፀሙ የሚያሳዩ ዘገባዎች እየወጡ ነው ይላል አምነስቲ።

በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ወኪሎችና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በለቀቁት መግለጫ “እየጨመረ የመጣው በሕፃናትና አዋቂ ሴቶች ላይ የሚፈፀም ወሲባዊ ጥቃት” እንዳሳሰባቸው “ለዚህ ጥቃት የተሰጠው ምላሽ በቂ እንዳልሆነ” ገልፀዋል ይላል አምነስቲ።

በሌላ በኩል የሰብዓዊ እርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ሆስፒታሎችና ሌሎች የጤና ተቋማት ጥቃት እንደደረሰባቸውና እንደተዘረፉ ዘግበዋል ይላል የመብት ተሟጋቹ አምነስቲ።

“ዓለም እየተመለከተ በትግራይ ያሉ አዋቂና ታዳጊ ሴቶች ወሲባዊ ጥቃት እየተጋረጠባቸው መሆኑ ትክክል አይደለም። ሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎችና ሆስፒታሎች አቅርቦታቸው በግጭቱ ምክንያት በመጎዳቱ የእርዳታ አቅም የላቸውም” ይላሉ ዴፕሮስ ሙቼና ሲል ቢቢሲ በስፋት መግለጫውን ዳስሶታል።

አውሎ ሚድያ ሚያዚያ 26 / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ