በትግራይ “አሁን ያለው አሳሳቢ ሁኔታ ድርቅ ከተጨመረበት ሁላችንም በህይወት የመኖራችን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይገባል” -የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ

0
352

የግብርናውን ሴክተር ወደ ነበረበት ለመመለስ “120 ቢልዮን ብር” እንደሚያስፈልግ የቢሮው ኃላፊ ተናግረዋል የግብራና ሚኒስቴር ይሂን ያክል በር ያስፈልጋል ስለመባሉ አንደማያቅ ነው የገለፀው፡፡

በትግራይ የግብርናው ዘርፍ ስራዎች በአሁኑ ወቅት ካልተጀመሩ በሚቀጥሉት 5 እና 10 ዓመታት በዚህች ሀገር ታይቶ የማይታወቅ ‘ረሀብ’ ሊኖር እንደሚችል የትግራይ ጊዜያዊ መስተዳድር የግብርና ቢሮ ኃላፊ አባዲ ግርማይ (ዶ/ር) ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር አባዲ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ በክልሉ የተካሔደው ጦርነት በግብርናው ዘርፍ ላይ ያስከተለውን ጉዳት ፣ አርሶአደሩ የተጋረጠበትን ፈተና እና በክልሉ አሁን ያለውን የግብርና እንቅስቃሴ በተመለከተ ተናግረዋል፡፡

ጦርነቱ ያስከተለው ጉዳት የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አባዲ ግርማይ (ዶ/ር) ፣ ባለፈው ዓመት በትግራይ ክልል በተከሰተው የበረሃ አምበጣ መንጋ ምክንያት 1/4ኛ የሚሆነው የክልሉ ምርት መውደሙን ገልጸዋል፡፡ ከአምበጣው በመቀጠል ደግሞ በክልሉ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የአርሶአደሩ ምርት መቃጠሉን እና መዘረፉን ነው ያስታወቁት፡፡

ዶ/ር አባዲ የደረሰው ውድመት እጅግ ከባድ መሆኑን አንስተው ካለፈው የመኸር ወቅት የተሰበሰበ “ምንም ምርት እንደሌለ”ም ገልጸዋል፡፡

70 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ምርት ከምዕራብና ደቡብ ትግራይ እንደሚሰበሰብ የጠቀሱት የቢሮ ኃላፊው፣ “በምዕራብ እና ደቡብ ትግራይ የነበረ ገበሬ አካባቢው በአማራ ኃይል ከተያዘ በኋላ ንብረቱንና ቀዬውን ትቶ ፣ ገሚሱ ወደ ሱዳን ገሚሱ ደግሞ ወደ ሌሎች የትግራይ አከባቢዎች ተፈናቅሏል” ብለዋል፡፡

በሌሎች የክልሉ ክፍሎች የተሰበሰበው ምርትም ቢሆን “በኤርትራ ሰራዊት ተዘርፏል ፤ እናም ምንም የቀረ ነገር የለም ፤ የትግራይ ገበሬ ባዶ እጁን ቀርቷል፤ የሚበላው እንኳን የለውም” ብለዋል ኃላፊው፡፡ የኤርትራ መንግስት በቅርቡ ለተባበሩት መንግስታት በጻፈው ደብዳቤ ፣ የሀገሪቱ ወታደሮች ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን ይፋ ቢያደርግም በወንጀል ድርጊት ግን አለመሳተፉን ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡

የግብርና ቢሮ ኃላፊው ዶ/ርአባዲ የትግራይ ገበሬን ሁኔታ ሲያስረዱ “የትግራይ ህዝብ ቤት ንብረቱ ተዘርፏል፤ ቋሚ ተክል እንኳን ሳይቀር ነው የወደመው” በማለት ገልፀዋል፡፡ የክልሉ አርሶአደር ያለበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ እንደሚያስጨንቃቸውም ነው ዶ/ር አባዲ የሚያስረዱት፡፡

አክለውም “ዘንድሮ ከመጪው ግንቦት ወር መጀመርያ አንስቶ የሆነ ነገር ማድረግ ካልተቻለ ፣ ለሚቀጥሉት 5/10 ዓመታት በዚህች ሀገር ታይቶ የማይታወቅ ረሀብና ቸነፈር ይኖራል” ሲሉም ያላቸውን የገዘፈ ስጋት አስቀምጠዋል፡፡

“አሁን ያለው አሳሳቢ ሁኔታ ድርቅ ከተጨመረበት ሁላችንም በህይወት የመኖራችን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፤ይህ ምንም ማመንታት የማያስፈልገው እውነታ ነው፡፡ ህይወት መቀጠል አለበት፤ ይህ ፖለቲካ አይደለም፡፡ ቢያንስ ለሚቀጥለው ዓመት ዘር መኖር አለበት፡፡ ገበሬው ተስፋ ማግኘት አለበት” ሲሉም ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡

“በገበሬው ላይ የደረሰው ችግር እጅግ ከባድ ነው፡፡ የሚያሳዝነው አርሶ አደሩ ለማረስ የሚሆን በሬ እንኳን የለውም” ብለዋል ዶ/ር አባዲ፡፡

በሚኒስቴር መስርያ ቤቱ የእርሻ ልማት ዘርፍ ተወካይ ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ግርማሜ ጋሩማ “በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ክልል የነበረው ሁሉም ምርት ወድሟል” ስለመባሉም ይሁን “ግብርናውን ወደ ነበረበት ለመመለስ 120 ቢሊዮን ብር የገንዘብ መጠን ያስፈልጋል” ስለተባለው ነገር የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትር ዴዔታው አክለውም ለትግራይ ክልል ለመጪው የመኸር ወቅት ለእርሻ ስራ የሚውሉ የምርጥ ዘር ፣ የአፈር ማዳበሪያ እና ሌሎች የግብርና ግብዓቶ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

“የክልሉ ግብርና ቢሮ የጠቀሰው ችግር በተባለው ልክ ካለም ፣ በአጠቃላይ ትግራይን መልሶ ለመገንባት በሰላም ሚኒስቴር የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ ስላለ በዚያ በኩል ለችግሩ ምላሽ ሊሰጥ ይችላል”ም ነው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው።

አውሎ ሚድያ ሚያዚያ 15 ዜና / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ