መሀመድ ዴክሲሶ ያለበት ቦታ አይታወቅም ተባለ

0
266

የካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በሚያስመርቅበት መድረክ የእነ አቶ ጃዋር መሃመድን በመጥራት ከእስር እንዲፈቱ የጠየቀው መሃመድ ዴክሲሶ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥሯል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ክስ ከተመሰረተበት ወዲህ ከእስር አልተለቀም።

የመሀመድ ቤተሰቦች ፥ ፍርድ ቤት ከአንድም ሁለት ጊዜ ቢያሰናብተውም እስካሁን ሳይለቀቅ ቀርቷል ብለዋል።

የመሀመድ ወንድም አቶ ሱልጣን ዴክሲሶ ለጀርመን ድምፅ እንደተናገሩት ከሆነ ፥ አሁን ላይ መሀመድ ዴክሲሶ ያለበትን ቤተሰቦቹ አያውቁም ብለዋል።

አቶ ሱልጣን ዴክሲሶ፥ ” በምርቃት ቀኑ እዛው በመድረክ ላይ ድምፁን ካሰማ በኃላ ነው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው፤ ከዛም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ነው የተወሰደው ፤ ከዛ ፍርድ ቀርቦ ነበር፤ ከዛ በኃላ ባልታወቀ ምክንያት ልዩ ኃይል በሚባለው ተወሰደ፤ ከተወሰደ ወዲህ ዛሬ 3 ሳምንት አልፎታል፤ እዚህ ነው ያለው፤ በዚህ ሁኔታ ነው ያለው የሚለውን እንደቤተሰብ እኛ ምንም የምናውቀው ነገር የለም” ብለዋል።

መጋቢት 7 በጅማ ከተማ ፍርድ ቤት በነፃ በራሱ ዋስ ከእስር እንዲለቀቅ ከተወሰነ ወዲህ ለሁለት ሳምንት ያለምንም ጥያቄ መሀመድ በጅማ ፖሊስ በእስር ላይ መቆየቱን አቶ ሱልጣን ተናግረው መጋቢት 23 ሲወጣ እንደገነ መታሰሩን ተናግረዋል።

አቶ ሱልጣን የነበረውን ሁኔታ ሲገልፁ ፥”በራሱ ዋስትና እንዲወጣ የተወሰነው መጋቢት 7 ነው እስከ መጋቢት 23 ግን እዛው ነው የቆየው ፤ እዛው እየተመላለስን እየጠየቅን ነበር፤ በመጋቢት 27 የሰው ዋስ አቅርቡ አሉ አቀረብን፤ መታወቂያውን ኮፒ አድርጎ ፈርሞ ልጁም አሻራውን ሰጥቶ ልክ ከእስር ቤት እንደወጣ ከጊቢው ሳይወጣ ነው የተጠለፈው። የጠለፈው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ነው 6 ሆነው መጥተው ነው በፓትሮል የወሰዱት ከዛ ቀን ጀምሮ እዚህ ነው የሚል ተጨባጭ መረጃ የለንም፤ ለምን እንደደበቁት ነው ግራ የገባን” ብለዋል።

አሁን ላይ መሀመድ የታሰረበትን /የሚገኝበት ደብዛው ከጠፋ 3 ሳምንታት አልፈዋል።

አቶ ሱልጣን ፥ መሀመድ ሲታሰርበት የነበረውን ፖሊስ ጣቢያ ቤተሰብ ሄዶ ሲጠይቅ “እኛ ፈተናል አናውቅም ነው፤ እኛ ፈተነዋል አይመለከተንም ነው” ያሉን ብለዋል።

አክለውም ፥ “…እዛ ያለው ሰብዓዊ መብት ከኛ የተሻለ አቅም ስላለው እንዲከታተል አድርገናል፤ እነሱም ማግኘት አልቻሉም። በተደጋጋሚ በደብዳቤ ሄደው እንደጠየቁ ነግረውናል፤ አለ ምንም እይሆንም እመኑን ነው እንጂ እነሱም በአይን ማየት እንዳልቻሉ ነው የሰማነው” ሲሉ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አማካሪ ኢማድ አብዱልፈታህ እንደተናገሩት መሀመድ ዴክሲሶ አሁን ያለበትን ስፍራ ለማወቅ የተለያዩ የመንግስት መዋቅሮችን ጠይቆ ለመረዳት ቢሞከርም ይህ ከኮሚሽኑ አቅም በላይ ነው ብለዋል።

አቶ አሚድ ፥ “…ፍርድ ቤት ከእስር እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ቢሰጥም ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ታስሮ ነው የቆየው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከጣቢያው ተለቋል ከተባለ በኃላ በሌላ የፖሊስ መኪና የት እንደተወሰደ አይታወቅም። የተለያዩ አካላትን አነጋግረን ያለበትን ቦታ ለማውቅ ጥረት ብናደርግም እስካሁን ያለበት ቦታ እዚህ ነው ብሎ ያሳየን አካል የለም፤ እኛም ያለበትን ቦታ ማወቅ አልቻልንም” ብለዋል።

አውሎ ሚድያ ሚያዚያ 15 ዜና / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA

ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ