ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነት ሰንጠረዥ አንድ ደረጃ ዝቅ አለች

0
228

በየዓመቱ የሃገራትን የፕሬስ ነፃነት ደረጃ እየመዘነ የሚሰፍረው ዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ኢትዮጵያ ከአምናው ደረጃዋ ዝቅ ብላለች ብሏል።

ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን፣ አርኤስኤፍ በተሰኘ ቅፅል ስሙ የሚታወቀው ድርጅት የዘንድሮውን [2021] የፕሬስ ነፃነት ደረጃ አውጥቷል።

ድርጅቱ 180 የዓለማችን ሃገራትን አካትቶ በሠራው ጥናት መሠረት ጋዜጠኝነት 70 በመቶ እክል ገጥሞታል ብሏል።

‘የተዛባ መረጃ ክትባት የሆነው ጋዜጠኝነት’ በ73 ሃገራት ከበድ ያለ እክል ገጥሞታል ይላል ድንበር የለሹ ድርጅት።እንደ አርኤስኤፍ (ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን) ዘገባ ጋዜጠኝነት ዘንድሮ በበርካታ ሃገራት ከበድ ያለ ችግር ገጥሞታል።

ድርጅቱ ሃገራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተገን አድርገው ጋዜጠኞች ተዘዋውረው እንዳይዘግቡ ከልክለዋል ሲል ይወቅሳል።ጥናቱ እንደሚጠቁመው በተለይ በእስያ፣ መካከለኛው ምስራቅና አውሮፓ ጋዜጠኞች ተዘዋውረው ለመዘገብ እየተቸገሩ ነው።

ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ማሕበር የበርካታ ሃገራት ባለሥልጣናት የተሳሳተ ዘገባ ሲያስተላልፉ ጋዜጠኞች ግን ትክክለኛውን መረጃ በማቅረብ ይህን ሲያርሙ ነበር ይላል።ድርጅቱ 111ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ብራዚል ፕሬዝደንት እና 148ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ቭኔዙዌላ መሪ ኒኮላስ ማዱሮ ኮሮናቫይረስን በተመለከተ የተናገሩትን ያልተረጋገጠ ወሬ እንደ ምሳሌ ጠቅሷል።

174ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢራን የፕሬስ ነፃነትን የበለጠ በመጨቆን ስሟ ተጠቅሷል። የፕሬዝደንት አብድል ፋታህ አል-ሲሲ ሃገር ግብፅም በኮሮናቫይረስ ዘመን የፕሬስ ነፃነትን በመግፈፍ 166ኛ ላይ ተቀምጣለች።

ኖርዌይ ለፕሬስ የላቀ ነፃነት በመስጠት ለአምስተኛ ተከታታይ ዓመት የአንድ ደረጃን ተቆጣጥራለች። ፊንላንድ ሁለተኛ፤ ስዊድን ደግሞ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በዶናልድ ትራምፕ ዘመን በርካታ ጋዜጠኞች ላይ ጥቃት የተሰነዘረባት የተባለችው ዩናይትድ ስቴትስ አንድ ደረጃ ቀንሳ 44ኛ ላይ ስትገኝ ድርጅቱ ፕሬስ ጨቋኝ ናት ሲል የፈረጃት ቻይና 177ኛ ላይ ትገኛለች።

የመጨረሻውን ሶስት ደረጃ የያዙት ተርከሜኒስታን [178ኛ]፣ ሰሜን ኮሪያ [179ኛ] እንዲሁም ኤርትራ [180ኛ] ናቸው።በ2021 ጥሩ መሻሻል አሳይተው በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ ብለው የተገኙት ሃገራት ቡሩንዲ፣ ሲራሊዮንና ማሊ ናቸው።ኢትዮጵያ በዘንድሮው የፕሬስ ነፃነት ሰንጠረዥ ላይ ሁለት ደረጃ ቀንሳ 101 ሆና ተገኝታለች።

ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ታይቶ የነበረው የፕሬስ ነፃነት አደጋ ተጋርጦበታል ይላል።

ቡድኑ የጋዜጠኞችና ጦማሪዎች ከእሥር መፈታትን እንደ መልካም እርምጃ ቢቆጥረውም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚከሰቱ ግጭቶች ሚድያው ፅንፍ እንዲይዝ እያደረገው ነው ይላል።

ኢትዮጵያ በ2020 ከ19 በላይ ጋዜጠኞችን ያለ ተጨባጭ ምክንያት ለእሥር ዳርጋለች የሚለው ድርጅቱ አንዳንድ ጋዜጠኞች የት እንዳሉ ሳይታወቅና ጠበቃ ሳይቀርብላቸው ቆይተዋል ሲል ይወቅሳል።

ግጭት ያለባቸው አካባቢዎች ሄዶ ለመዘገብ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል የሚለው ቡድኑ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥንም እንደ አንድ እክል አንስቷል ሲል ቢቢሲ ዘግቧታል።

አውሎ ሚድያ ሚያዚያ 12 ዜና / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA

ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ