የኤርትራ ወታደሮች መውጣታቸውን የሚያረጋግጥ ምስክር አላገኘሁም – የአውሮፓ ልዩ ልዑክ

0
387

“በጉብኝቴ ወቅት የኤርትራ ወታደሮች መውጣታቸውን የሚያረጋግጥ ምስክር ማየትም ሆነ መስማት አልቻልኩም። እንዲያውም በአንዳንድ የትግራይ ቦታዎች ማጠናከሪያ እንደተጨመረላቸው የሚገልጽ የተወሰነ መረጃም አግኝቻለሁ” ሲሉ የአውሮፓ ኅብረት ልዩ ልዑክ ፔካ ሐቪስቶ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከቀናት በፊት ወታደሮቹ መውጣት መጀመራቸውን ገልጻ ነበር

ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ አቅንተው ትግራይን የጎበኙት የአውሮፓ ኅብረት ልዩ ልዑክ ፔካ ሐቪስቶ መንግሥት ያፋ ባደረገው መሠረት የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ለመውጣታቸው ማረጋገጫ እንዳላገኙ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ለቡድን ሰባት አገራት የውጭ ጉዳይ ምኒስትሮች መግለጫ በሰጠው ምላሽ “በህወሓት ተቆስቁሰው ድንበር የተሻገሩት የኤርትራ ወታደሮች ለቀው መውጣት ጀምረዋል” ብሎ ነበር።

በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት የአውሮፓ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ፔካ ሐቪስቶ “በጉብኝቴ ወቅት የኤርትራ ወታደሮች መውጣታቸውን የሚያረጋግጥ ምስክር ማየትም ሆነ መስማት አልቻልኩም።

በተቃራኒው በትግራይ እና በመቐለ ጉብኝቴ ያነጋገርኳቸው ኤርትራውያን በትግራይ መገኘታቸውን ነግረውኛል። እንዲያውም በአንዳንድ የትግራይ ቦታዎች ማጠናከሪያ እንደተጨመረላቸው የሚገልጽ የተወሰነ መረጃም አግኝቻለሁ” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ከተደጋጋሚ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ማስተባበያዎች በኋላ የኤርትራ ወታደሮች ድንበር አቋርጠው ወደ ትግራይ መግባታቸውን ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያረጋገጡት መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ነው።

የኤርትራ ወታደሮች “ያለ ቅድመ-ሁኔታ በፍጥነት” ከኢትዮጵያ ሊወጡ እንደሚገባ የጠየቁት የቡድን ሰባት አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ምኒስትሮች ሒደቱ “ሊረጋገጥ የሚችል” መሆን አለበት ብለዋል።

የኤርትራ መንግሥት እስካሁን ድረስ ወታደሮቹ ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ ስለመግባታቸው በይፋ ማረጋገጫ አልሰጠም።

ዶይቼ ቬለ ወደ ይህንን በተመለከተ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚነስትር ጽ/ቤት ቢደወልም በኢሜል ቢጻፍላቸውም መልስ አልተሰጠም እንዲሁም ኤርትራ ማስታወቂያ ምኒስትር የማነ ገብረ መስቀል ቢሮ ያደረጋቸው የስልክ ጥሪዎች አልተነሱም።

የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቅ መልዕክት ይዘው ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት የአውሮፓ ልዩ ልዑክ ፔካ ሐቪስቶ ሲመለሱ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ቃለ መጠይቅ እንደተባለው ወጥተው ቢሆን ኖሮ እናውቅ ነበር ብለዋል።

ልዩ መልዕክተኛው እንደ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የቡድን ሰባት አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ምኒስትሮች ሁሉ ለትግራይ ቀውስ መፍትሔ ለማበጀት የኤርትራ ወታደሮች ለቀው ሊወጡ እንደሚገባ አቋማቸውን ገልጸዋል።

ፔካ ሐቪስቶ “እንዲህ አይነት ግጭቶች ማብቂያ የሚያገኙት በድርድር ብቻ ነው። ለመንግሥት፣ ለአማራ ሚሊሺያ፣ የደፈጣ ውጊያ ለገጠሙት እና ለኤርትራ ወታደሮች የምንሰጠው ምክር መጀመሪያ የኤርትራ ወታደሮች መውጣት አለባቸው። ከዚያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የኢትዮጵያ ባለድርሻዎች ሊደራደሩ ይገባል።

ግጭቱ በተራዘመ ቁጥር መደራደር አስቸጋሪ እየሆነ ይሔዳል። ምክንያቱም ወጣቶች ለደፈጣ ውጊያ እየተመለመሉ ነው። ወደ ፊትም ተጨማሪ ወጣቶች ሊቀላቀሉ ይችላሉ። ይኸ ደግሞ ጥሩ አይደለም። በመንግሥት፣ በሲቪክ ማህበራት እና በትግራይ ተወካዮች መካከል ሐቀኛ ውይይት ሊደረግ ይገባል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

አውሎ ሚድያ ሚያዚያ 08 ዜና / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com/category/zena/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ