ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳንን ባለሙያ ላኩ ማለቷ የዲፕሎማሲ ጥረቷን ጫፍ ያደረሰ ነው – ፕ/ር ያዕቆብ አርሰኖ

0
180

የኢትዮጵያ መንግሥት የግብጽና የሱዳን የግድብ ባለሙያዎቻቸውን (ኦፕሬተሮች) እንዲሰይሙ መጋበዟ ከዲፕሎማሲ ሙያ አንጻር ሲታይ ዲፕሎማሲውን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለማድረስ የተደረገ ሂደትና ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችውን የዲፕሎማሲ ጥረት ጫፍ ያደረሰና ኢላማውን የመታ ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ አስታወቁ፡፡

ፕሮፌሰር ያዕቆብ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሊት ከመጀመሩ በፊት መረጃ ለመለዋወጥ የግድብኦፕሬተሮቻቸውን እንዲሰይሙ ኢትዮጵያ ለግብጽና ለሱዳን ያቀረበችው ጥያቄ የዲፕሎማሲውን ጥረት ጫፍ ያደረሰ (ከፍ ያደረገ) እና ኢላማውን በአግባቡ የመታ መሆኑን ለአገራቱ የቀረበው ጥያቄ በዲፕሎማሲው መስከ የተደረገውን ጥረት የመጨረሻው ነጥብ ያስቆጠረ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ያዕቆብ ፤ ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ የግብጽና የሱዳን ባለሙያዎች፣ እንዲሁም የሱዳን መሪም ጭምር የህዳሴ ግድቡ ያለበት ቦታ ድረስ ሄደው ሲያዩና ሲከታተሉ እንደነበር አስታወሰዋል።

አሁንም ሁለቱ አገራት ባለሙያዎቻቸውን እንዲሰይሙ ሲጋበዙ የመጀመሪያ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡

ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ እየገነባች ያለው የህዳሴ ግድብ ድብቅ ነው የሚል እሳቤ ቢኖራቸውም፤ ይህ እንዳልሆነ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊትም በግልጽ ስታደርግ የነበረ ነው፤ አሁንም ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሊት ከመጀመሩ በፊት ሁለቱ አገሮች ባለሙያዎቻቸውን እንዲሰይሙ ጥሪ አቅርባለች ፡፡ ይህም ደግሞ ከዚህ ቀደምም ሲያዩ እንደቆዩ ሁሉ አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ በኩል በድብቅ የሚሰራ ሥራ አለመኖርን የሚያሳይ ነው ነው ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር ያዕቆብ እንዳሉት፤ ለግብጽና ሱዳን ግድቡ ከመነሻው ጀምሮ እየተሰራ ነው ተብሎ ሲነገራቸው ቆይቷል፤ ከተነገራቸው ወዲህ ደግሞ ቀደም ሲል አትችሉም ሲሉ ሰንብተዋል፡፡ ግድቡ እየተገነባ ከቆየ በኋላ ደግሞ ግድብ እንዲስተጓጎል ጥረዋል፡፡ ቀጥሎም የግድቡ ስራ እየተጠናቀቀ መሄዱን ሲረዱ በአግራሞት ሲመለከቱ ከርመዋል፡፡

በአሁን ደረጃ የኢትዮጵያ መንግስት ግብጽና ሱዳን የግድብ ባለሙያዎችን (ኦፕሬተሮችን) እንዲሰይሙ መፍቀዱ ከዲፕሎማሲው ሙያ አንጻር ሲስተዋል ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲውን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ማድረስ መቻሏ አመላካች ሆኗል ፡፡ ይህ ማለት እኛ ሥራችን በአደባባይ የተገለጠ እና ምስጢራዊ ያልሆነ መሆኑን ማሳያ ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ለእኛ የሚጠቅም መሆኑን ስንነግራቸው እንደቆየንና ለሁለቱም አገሮች ከዚህ ቀደም ሲነገራቸው እንደቆየው ሁሉ አሁንም ባለሙያዎችን እንዲመድቡ መጋበዛቸው እነሱንም በከፋ መንገድ የማይጎዳ መሆኑ ግልጽ እንዲሆንላቸው ከሚል ሐሳብ የመጣ ነው፡፡ ይህንኑ ያዩትን ነገር ለሕዝባቸው እንዲገልጹትም ከሚል እሳቤ የመነጨ እርምጃ ነው ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህም አካሄዷ ዲፕሎማሲውን ወደጫፍ ማድረስ መቻሏን አመልክተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ያዕቆብ፣ አሁን በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ብዙ ጫጫታ ባለበት በዚህ ሁኔታ እንኳ ውሃው ከመሞላቱ በፊት ባለሙያ ሰይሙ ብሎ ማለት በኢትዮጵያ በኩል የታየው ልበ ሙሉነትና ሆደ ሰፊነት መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል። ይህ የኢትዮጵያ አካሄድ ትክክለኛ እና ዲፕሎማሲውንም ውጤታማ በሆነ መልኩ ጫፍ ያደረሰ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሃ ከመሙላቷ በፊት ሱዳንና ግብጽ ለመረጃ ልውውጥ የግድብ ኦፕሬተሮቻቸውን እንዲሰይሙ ጥሪ ማቅረቧ የሚታወስ ሲሆን፤ ሁለተኛው የህዳሴ ግድቡን ውሃ የመሙላቱ ሥራም ሐምሌ እና ነሐሴ እንደ ውሃው የፍሰት መጠን ታይቶም ግድቡን ውሃ የመሙላቱ ሂደት እስከ መስከረም ሊቀጥል እንደሚችል ይታወቃል።

አውሎ ሚድያ ሚያዚያ 05 ዜና / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com/category/zena/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ