የአፍሪካ ሕብረት የሕዳሴ ግድብን ችግር መፍታት እንዳለበት ሩሲያ ገለፀች

0
125

በግድቡ ላይ “የሁሉንም ጥቅም የሚያረጋግጥ” ስምምነት መደረስ እንዳለበት የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለፀዋል፡፡

በግብፅ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ዛሬ ሰኞ ከግብፁ አቻቸው ሳሚ ሹክሪ ጋር በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመግለጫው ወቅት ፣ ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በግብፅ ፣ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል “የሁሉም ወገኖች ጥቅም የሚረጋገጥበት ስምምነት መደረስ አለበት” ብለዋል፡፡

ሩሲያ በድርድሩ ቴክኒካዊ ድጋፍ ለማድረግ ሀሳብ አቅርባ እንደነበር ያስታወሱት ሚስተር ላቭሮቭ ፣ ይሁንና በተደራዳሪ ሀገራት መልስ እንዳልተሰጣት ነው ያነሱት፡፡ “የአፍሪካ ሕብረት የሕዳሴ ግድብን ችግር መፍታት አለበት” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹክሪ በበኩላቸው “በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በመተማመን ላይ ነን” ብለዋል፡፡ ከግድቡ ጋር ያለውን አለመግባባት ሩሲያ መገንዘቧን የገለጹት ሚኒስትሩ ፣ ሩሲያ በግድቡ ዙሪያ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ወሳኝ ሚና መጫወት እንዳለባትም ነው የተናገሩት፡፡

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋርም በካይሮ ውይይት አድርገዋል፡፡

ላቭሮቭ በካይሮ ቆይታቸው ከአረብ ሊግ ዋና ፀሀፊ አህመድ አቦል ጌት ጋርም ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በቅርቡ በኪንሻሳ የተካሄደው ውይይት ፣ በቀጣይነት ማን ያደራድር በሚለው ጉዳይ ዙሪያ ስምምነት ሳይደረስ ያለውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ስምምነት ላለመደረሱ ግብፅ እና ሱዳን ኢትዮጵያን ተጠያቂ ሲያደርጉ ፣ ኢትዮጵያ በበኩሏ ሁለቱን ሀገራት ተጠያቂ አድርጋለች፡፡ ሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ፣ ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ አሜሪካ ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የተባበሩት መንግስታት በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ የሚፈልጉ ሲሆን ፣ ይህን የግብፅ እና የሱዳን አቋም “የአፍሪካ ሕብረትን ማሳነስ እና መናቅ ነው” የምትለው ኢትዮጵያ ፣ ከአህጉራዊው ህብረት ውጭ ያሉ አካላት ከታዛቢነት ያለፈ ሚና እንዲኖራቸው እንደማትፈልግ አስታውቃለች፡፡

በሁለተኛው የግድቡ ሙሌት ዙሪያ መረጃ ለመለዋወጥ ፣ ግብፅ እና ሱዳን ባለሙያዎችን እንዲመድቡ ኢትዮጵያ ጥያቄ ብታቀርብም ፣ ሁለቱ ሀገራት ጥያቄውን እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ ኢትዮጵያ በመጪው ክረምት የግድቡን ሁለተኛ ሙሌት እንደምታከናውን በያዘችው አቋም ፀንታ የቀጠለች ሲሆን የግብፅ መሪዎችም በኢትዮጵያ ላይ ዛቻቸውን ቀጥለዋል ሲል አል ዐይን ዘግቧል፡፡

አውሎ ሚድያ ሚያዚያ 04 ዜና / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com/category/zena/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ