ህዳሴ ግድብ፡ ሱዳንና ግብጽ የኢትዮጵያን ጥሪ ሳይቀበሉት ቀሩ

0
77

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ከመጀመሯ በፊት መረጃ ለመለዋወጥ እንዲቻል ግብጽና ሱዳን ባለሙያዎችን እንዲሰይሙ ያቀረበችው ጥሪ አገራቱ ሳይቀበሉት እንደቀረ ተዘገበ።

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በያዘችው መርሃ ግብር መሠረት ሁለተኛውን ዙር የግድቡን የውሃ ሙሌት በመጪው የክረምት ወር እንደምታካሂድ ገልጻ ነው አገራቱን ባለሙያዎቻቸውን እንዲያሳውቁ የጠየቀችው።

ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ እየገነባቸው ያለውን ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫን በተመለከተ አስገዳጅ ሕጋዊ ስምምነት ላይ ሳይደረስ የውሃ ሙሌት እንዳይካሄድ አጥብቀው ሲወተውቱ መቆየታቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያ የሱዳንና የግብጽን ጥያቄ በተደጋጋሚ ውድቅ ያደረገችው ሲሆን ግድቡን ውሃ እንዲይዝ የማድረጉ ሥራ በአገራቱ መካከል የሚደረገው ድርድር እየተካሄደም ቢሆን የማይቀር እንደሆነ ስትገልጽ ቆይታለች።

ባለፈው ሳምንት የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር በሆነችው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰብሳቢነት ኪንሻሳ ላይ የተካሄደው ድርድር ያለ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ ኢትዮጵያ ስለሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ከሱዳንና ግብጽ ጋር መረጃ ለመለዋወጥ እንዲያመች ባለሙያዎቻቸውን እንዲያሳውቁ ጠይቃለች።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ከካይሮ እንደዘገበው ግብጽና ሱዳን ከኢትዮጵያ የቀረበላቸውን ጥሪ ተከትሎ አገራቱ ሲያቀረቡ የቆየው ሕጋዊና አሳሪ ስምምነት ላይ ሳይደረስ መረጃ ለመለዋወጥ የሚያግዙ ባለሙያዎችን እንዲያሳውቁ የቀረበውን ጥያቄ አልተቀበሉትም።

የሱዳን ዜና ወኪል የአገሪቱ የውሃ ሚኒስቴር መግለጫን ጠቅሶ እንደዘገበው በግድቡ ሙሌት ላይ የመረጃ ልውውጡ አስፈላጊ አካሄድ እንደሆነ ጠቅሶ ነገር ግን ከስምምነት ላይ ከተደረሰው ክፍል ውስጥ በተወሰኑት ላይ የሚያተኩር መሆኑ ጥርጣሬን እንደፈጠረ ገልጿል።

አገራቱ ኢትዮጵያ አከናውነዋለሁ ያለችው ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተመለከተ ስምምነት ሳይደረስ እንዳይካሄድ በተደጋጋሚ ተቃውሟቸውን ቢያሰሙም የማይቀር መሆኑን በመገንዘብ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ታውቋል።

በሱዳን በኩል 600 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የሚይዘውን የጀበል አወልያ የውሃ ማከማቻ ግድብን፣ ለመጠጥ ውሃና ለግብርና የሚያስፈልጋትን ውሃ መጠን ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር ሙሌት ከመጀመሯ በፊት እንደምትሞላ ሱና ዘግቧል።

የግብጽ የመስኖ ሚኒስትርም ለአንድ የአገሪቱ ቴሌቪዥን ኢትዮጵያ የምታካሂደውን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በግዙፉ የአሰዋን ግድብ ውሃ እንደሚያካክሱት ገልጸው፤ ዋና ስጋታቸው የድርቅ ወቅት እንደሚሆን ማመልከታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የሆኑት ስለሺ በቀለ (ዶ/ር፣ ኢንጂ.) ኢትዮጵያ ወደ መጠናቀቁ የተቃረበውን የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ እንደማታራዝመውና ለዚህም የሚያበቃ አሰራርና ምክንያትም እንደሌለ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም መጋቢት ወር ላይ ለአገሪቱ ምክር ቤት ላይ እንዳስረዱት፤ ኢትዮጵያ የግድቡን ውሃ አሞላል በተመለከተ ከድርድሩ ማብቃት በኋላ ይከናወን የሚባል ከሆነ አገሪቱን “በዓመት አንድ ቢሊየን ዶላር ያሳጣታል” በማለት የውሃ ሙሌቱን ማዘግየት እንደማይቻል አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሌት ያከናወነችው ተመሳሳይ የሆነ ጥያቄ ከሱዳንና ግብጽ እየቀረበ በነበረበት ጊዜ መሆኑ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ አምስት ቢሊየን የሚጠጋ ዶላር አውጥታ እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሊጠናቀቅ 20 በመቶ ያህል የቀረው ሲሆን፤ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ካሉ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ሁሉ ቀዳሚው ይሆናል ተብሏል።

ግድቡ ተጠናቅቆ ሙሉ ለሙሉ ሥራውን ሲጀምር ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም አለው።

ግድቡ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ያደረገ ሲሆን ሁለተኛውን ዙር ደግሞ በመጪው ክረምት ሐምሌና ነሐሴ እንዲሁም አስፈላጊ ከሆነ በመስከረም ወር ላይ እንደሚከናወን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።

ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው የግድቡ የግንባታ ሥራ መከናወኑ የተነገረ ሲሆን በመጪው ዓመትም በተወሰነ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል።

ግብጽና ሱዳን ግድቡ የውሃ አቅርቦታችንን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል በሚል ከግንባታው መጀመር አንስቶ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቢቆዩም፤ ከግማሽ በላይ ለሚሆነው ሕዝቧና እያደገ ላለው የኢንዱስትሪ ዘርፏ ኤሌክትሪክ ለማቅረብ ዋነኛ ግቧ አድርጋ የተሳችው ኢትዮጵያ በግንባታውና ቀጥላ ወደ ማጠናቀቁ ተቃርባለች።

የግብጽና የሱዳን መንግሥታት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተለያዩ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው ግድብ ሳቢያ አገሮቻቸው ከወንዙ በሚያገኙት የውሃ መጠን ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረው ስጋታቸውን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን የምትጠቀመው ውሃውን በግዛቷ ውስጥ ለሚያስቀሩ ፕሮጀክቶች እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ብታስረዳም ሱዳን በተለይም ግብጽ የትኛውም አይነት በውሃው ላይ የሚከናወን ሥራ የእነርሱን ስምምነት ሳያገኝ መካሄድ እንደሌለበት ሲገልጹ ቆይተዋል።

ግንባታው ከተጀመረ አስረኛ ዓመቱን የያዘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና ቀጣይ የሥራ ሂደትን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል ለዓመታት ሲካሄድ የቆየው ድርድር ውጤት ሳያስገኝ እስካሁን ዘልቋል።

የአፍሪካ ሕብረት የሚያሸማግለው ይህ ድርድር ቀደም ሲል በአዲስ አበባ፣ በካርቱም፣ በካይሮና በዋሽንግተን ላይ የሦስቱ አገራት ልዑካን ተገናኝተው ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ ከቆየ በኋላ በበይነ መረብ አማካይነት ቀጥሎ ነበር።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በታላቁ የሕዳሴው ግድብ የውሃ አሞላልና ቀጣይ ሂደት ላይ ለዓመታት ሲያካሂዱት የነበረው ድርድር ቀጣይ ባለፈው ሳምንት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዋና ከተማ ላይ ለሦስት ቀናት ተካሂዶ ያለውጤት ከተጠናቀቀ ከቀናት በኋላ ነበር ኢትዮጵያ አገራቱ ባለሙያዎቻቸውን እንዲሰይሙ ጥያቄ ያቀረበችው።

ምንጭ ቢቢሲ

አውሎ ሚድያ ሚያዚያ 04 ዜና / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com/category/zena/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ