በአፋር ክልል በተሰነዘረ ጥቃት በትንሹ 30 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

0
145

በአፋር ክልል ሀሩቃ በተባለ ቦታ ባለፈው አርብ በተሰነዘረ ጥቃት በትንሹ 30 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ50 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች መቁሰላቸውን የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ጥቃቱን ፈጸሙ የተባሉት የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በዚያኑ ዕለት ምሽት ገዋኔ በተባለ ቦታ በከፈቱት ተኩስ ሁለት የክልሉ መንግስት ሰራተኞች መገደላቸውንም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

የአፋር ክልል የፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ አቶ አህመድ ሁመድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ ወደ ክልላቸው ዘልቆ የገባው የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል፣ በሀሩቃ ቀበሌ ጥቃቱን የፈጸመው ከሁለት ቀን በፊት፤ መጋቢት 25፤ ከቀኑ 9 ሰዓት ገደማ ነው። የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ወደ ቀበሌዋ ገብተው ተኩስ መክፈታቸውን የሚገልጹት ምክትል የፖሊስ ኮሚሽነሩ፣ በጥቃቱም “ከ30 በላይ ንጹሃን ዜጎች ተረሽነዋል” ብለዋል።

በአርቡ ጥቃት ከተገደሉት ውስጥ ሴቶች እና ህጻናት እንደሚገኙበት የጠቀሱት አቶ አህመድ፤ ከ50 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች መቁሰላቸውንም አስረድተዋል። በጥቃቱ የተጎዱት ሰዎች በሎጊያ እና ዱብቲ በሚገኙ ሆስፒታሎች በአሁኑ ወቅት የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑንም አመልክተዋል። 

የአፋር ክልል ልዩ ኃይል ጥቃት ሲፈጽም ነበር ያሉትን አንድ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባል “እጅ ከፍንጅ” መያዛቸውን የሚናገሩት አቶ አህመድ፤ ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት “በፖሊስ ቁጥጥር ስር” እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ሁኖም የሶማሌ ክልል ጥቃቱ የተፈጸመው “በክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ነው” የሚለውን ውንጀላ አስተባብሏል። 

በሀሩቃ እና በገዋኔ ተፈጸሙ ስለ ተባሉ ጥቃቶች የተጠየቁ አንድ የሶማሌ ክልል የመንግስት ሰራተኛ፤ የአፋር ክልል ላደረሰው ጥቃት ምላሽ ከመስጠት በዘለለ “የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በነዋሪዎች ላይ ጥቃት አልፈጸመም” ሲሉ አስተባብለዋል ዘገባው የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው፡፡

አውሎ ሚድያ መጋቢት 28 ዜና / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com/category/zena/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ