በትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠበት ምክንያት አልታወቀም – የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል

0
349

በትግራይ ክልል ካለፈው ሀሙስ ጀምሮ የመብራት አገልግሎቱ የተቋረጠበት ምክንያት እስካሁን አለመታወቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገልጿል፡፡

ክልሉ በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ውስጥ ከተከ ዘ ኃይል ማመንጫ አገልግሎት እንደሚያገኝ ተቋሙ አስታውቋል

በትግራይ ክልል ካለፈው ሀሙስ ከሰዓት ጀምሮ የመብራት አገልግሎት መቋረጡን የመቀሌና አካባቢዋ ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡

ነዋሪዎቹ እንደገለፁት ፣ በክልሉ ከነበረው ውጊያ በኋላ የመብራት መቆራረጥ ቢያጋጥምም የአሁኑ ግን ረዘም ላሉ ቀናት መቆየቱንና መቼ አገልግሎት እንደሚጀምር መረጃ እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከባለፈው ሀሙስ ዕለት ጀምሮ በትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ መቋረጡን አረጋግጠዋል፡፡

የመብራት አገልግሎቱ የተቋረጠበትን ምክንያት ለመለየትም የጥገና ባለሙያዎች ከአርብ ዕለት ጀምሮ በመስመሩ ላይ ፍተሻ እያደረጉ መቆየታቸውን ገልጸው “በትክክል እዚህ ቦታ ላይ ይህ ችግር ነው ያጋጠመው” የሚል ሪፖርት እስካሁን አለመቅረቡንና ችግሩ በውል አለመታወቁን አስታውቀዋል፡፡ አሁን ላይ በትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ እንደማይሰራ እንጂ ለምን እንደማይሰራ የታወቀ ነገር እንደሌለ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡

ክልሉ ከአላማጣ መሆኒ መቐለ በተዘረጋ መስመር ኤሌክትሪክ ሲያገኝ እንደነበር የገለጹት አቶ ሞገስ ፣ ከተከዘ መስመር ያለው አማራጭም ለጊዜው አገልግሎት እየሰጠ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ከአላማጣ እስከ መቐለ ባለው የኤሌክትሪክ መስመር ላይ ፍተሻ ተከናውኖ የጥገና ስራውን እንደሚከናወንም አቶ ሞገስ ገልጸዋል፡፡

አቶ ሞገስ፣ ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው ከተከዘ ኃይል ማመንጫ ወደ መቐለ የነበረው መስመር የጥገና ስራው እስካሁን ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ጥገናው አልቆ በጥቂት ቀናት ውስጥ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡

አሁን የተፈጠረውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግር መለየት እስኪቻል ድረስ ከተከዜ መቐለ ባለው የኤሌክትሪክ መስመር ፣ በአንድ ወይም በሁለት ቀናት ውስጥ ክልሉ መብራት እንደሚያገኝም ነው የተናገሩት፡፡

ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ለከፋ ጉዳት የሚዳረገው ሕዝቡ በመሆኑ፣ የመብራት መቋረጡ “ሆን ተብሎ የሚፈጸም” ከሆነ በቅርብ ያለው ሕዝብ ሊያስቆም እንደሚገባ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

አውሎ ሚድያ መጋቢት 28 ዜና / 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com/category/zena/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ