ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ሠራተኞች ትግራይ ውስጥ ሰዎች ሲገደሉ ማየታቸውን ተናገሩ

0
494

ድንበር የለሸ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) የተባለው ግብረሰናይ ድርጅት ትግራይ ውስጥ ማክሰኞ ዕለት አራት ሰዎች በኢትዮጵያ ወታደሮች ሲገደሉ ሠራተኞቹ መመልከታቸውን ገለጸ።

ግብረሰናይ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ሠራተኞቹ ከክልሉ ዋና ከተማ መቐለ ወደ አዲግራት በሚወስደው መንገድ ላይ እየተጓዙ ሳለ በወታደሮች የተፈጸመውን ግድያ መመልከታቸውን ገልጿል።

“ወታደሮቹ በሚኒባስ ተሽከርካሪዎች ሲጓዙ የነበሩ ሰዎችን አስገድደው እንዲወርዱ ካደረጉ በኋላ ሴቶቹን ከወንዶቹ ለይተው እንዲሄዱ ፈቀዱላቸው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወንዶቹ በጥይት ተመተው ተገደሉ” ሲል መግለጫው ሁኔታውን ያብራራል።

“ይህ የተከሰተው የታጠቀ ቡድን በኢትዮጵያ ሠራዊት ተሽከርካሪዎች ላይ የደፈጣ ጥቃት የሚመስል ድርጊት ከተፈጸመ በኋላ” እንደሆነ ድርጅቱ ሠራተኞቹ መመልከታቸውን አስፍሯል።

ኤምኤስኤፍ በኢትዮጵያ ወታደሮች በደረሰው ጥቃት የሞቱ እና የቆሰሉ ሰለመኖራቸው ሠራተኞቹ መመልከታቸወን ጨምሮ ገልጿል።

የኤምኤስኤፍ ሠራተኞች በስፍራው ሲደርሱ “ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በእሳት እየነደዱ ነበር” ሲሉ ገልጸዋል ብሏል።

የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን የኮምዩኒኬሽን መሪ ሶፊ ማደን ለቢቢሲ እንደተናገሩት አራቱ ወንዶቹ የተገደሉት ከሴት ተሳፋሪዎች ከተለዩ በኋላ ነው።

“ሠራተኞቻችን በቀጥታ መመልከት የቻሉት አራቱን ብቻ ነው። ከዕይታ ውጭ የሆኑ ሌሎች ሊኖሩ ይችላሉ” ብለዋል።

አክለውም “አስከምናውቀው ድረስ የተገደሉት ሰዎች ከመኪናው የወረዱ ሲሆኑ፤ የደንብ ልብስ ያልለበሱና ከሕዝብ ማመላለሻ መኪናው የወረዱ ናቸው” ያሉት ሶፊ ማደን፤ “ሟቾቹ ከዚህ ወይም ከዚያኛው ወገን ናቸው ለማለት አንችልም” ብለዋል።

ድርጅቱ በመግለጫው ላይ በግጭት ወቅት ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።

በዚህ ጉዳይ አስካሁን መንግሥት ያለው ነገር የለም። ቢቢሲም ከመንግሥት በኩል ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ይህ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) የተባለው በህክምና ላይ የሚሰራው የበጎ አድራጎት ድርጅት ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል የተካሄደውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ በሕክምና ተቋማት ላይ ሆን ተብሎ ዘረፋ እና ጥቃት ተፈጽሟል ብሎ ነበር።

ባለፈው ማክሰኞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትግራይ ውስጥ በተከሰተው ግጭት በደልና ዘረፋ እንደተከሰተ ገልጸው፤ በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ ወታደሮች ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በአክሱም ከተማ ተፈጸሙ ስለተባሉ ግድያዎች በሚመለከት ትናንት ረቡዕ ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ላይ የኤርትራ ወታደሮች በከተማዋ ውስጥ ከ100 በላይ ሰላማዊ ሰዎችን እንደገደሉ ባሰባሰበው መረጃ መሠረት ይፋ አድርጓል።

የህወሓት ኃይሎች በትግራይ ውስጥ በነበረው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ጦርነት ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ይነገራል።

አንዳንዶች ዓለም አቀፍና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በግጭቱ ሳቢያ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱና በመቶሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ከመኖሪያቸው እንደተፈናቀሉ ይናገራሉ።

አውሎ ሚድያ መጋቢት 17/ 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com/category/zena/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ