ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን ካላስተካከለ በምርጫው ላንሳተፍ እንችላለን- የሶማሊ ክልል መንግስት

0
732

ምርጫ ቦርድ በ 8 ቀበሌዎች ያሳለፈውን ውሳኔ ካልሻረ በምርጫው ለመሳተፍ እንደሚቸገር የሶማሌ ክልል ገለጸ፡፡

ቦርዱ በሶማሌ እና በአፋር ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በተነሳባቸው 8 ቀበሌዎች የምርጫ ጣቢያዎች እንዳይቋቋሙ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀደም ሲል የነበሩት አምስት ሀገራዊ ምርጫዎች ሲደረጉ በነበረው አግባብ የምርጫ ጣቢያዎችን የማይቋቋም ከሆነ በምርጫው ለመሳተፍ እንደሚቸገር የሶማሌ ክልል አስታወቀ፡፡

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በ 8 ቀበሌዎች ላይ ያቀረበውን አቤቱታ መነሻ አድርጎ ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቀበሌዎቹ ሊከፈቱ የነበሩ 30 የምርጫ ጣቢያዎች በአካባቢው እንዳይቋቋሙ መወሰኑ ይታወቃል፡፡

የቦርዱን ውሳኔ በመቃወም የሶማሌ ክልሉ ባወጣውመግጫ ፣ የክልሉ መንግስት በቦርዱ የተሰጠውን ውሳኔ እንደማይቀበል ገልጾ ውሳኔውን “ለአንድ ወገን ያደላና ኢ ፍትሐዊ ” ብሎታል፡፡

ከአሁን በፊትም የአፋር ክልል “በሶማሌ ክልል በሚገኙ ሦስት ከተሞች ወይም ቀበሌዎች ማለትም ገርባኢሲ (ገዳማይቱ)፣ አዳይቱ እና ኡንዱፍን ላይ የይገባኝል ጥያቄያቀርብ ነበረ” ብሏል መግለጫው፡፡ እነዚህን ሦስት ቀበሌዎች ጨምሮ ፣ አሁን በተወሰነው ውሳኔ የተካተቱት ተጨማሪ አምስት ቀበሌዎች “ከክልሉ ምስረታ ጀምሮ በሱማሌ ክልል ስር ሲተዳደሩ የቆዩ” መሆናቸውን የጠቀሰው መግለጫው የቦርዱ ን ውሳኔ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጿል፡፡

የሶማሌ ከልላዊ መንግስት በመግለጫው ፣ ክልሉ የካቲት 12 ቀን 2013 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ፣ የአፋር ክልል የይገባኛል ጥያቄ ያነሳባቸው 8 ቀበሌዎች ባለፉት አምስት ብሔራዊ ምርጫዎች በሶማሌ ከልል ሥር ሆነው የፈዴራል ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት ተወካዮች ምርጫ የተካሄደባቸው መሆኑን በመጥቀስ ፣ 6ኛው ብሔራዊ ምርጫም ቀድሞ በነበረው መሰረት እንዲከናወን መጠየቁን ገልጿል።

ይሁን እንጂ “ቦርዱ የሶማሌ ክልልን አስተያየት ሳይጠይቅና በደብዳቤ የተገለጸውን ጉዳይ ወደ ጎን ብሎታል” ሲል ክልሉ ከሷል፡፡ የቦርዱ ውሳኔ ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ እንዲሆን እየተደረገ ባለው ጥረት ላይ “አሉታዊ ተፅዕኖ“ እንደሚሳድርም ነው ክልሉ በመግለጫው ያነሳው፡፡

በመሆኑም የቦርዱ ውሳኔ ተሽሮ፣ የምርጫ ጣቢያዎቹ ቀደም ሲል እንደነበረው ካልተቋቋሙ በምርጫው ለመሳተፍ እንደሚቸገር የሶማሌ ክልል አስታውቋል፡፡

ቦርዱ ከሰሞኑ በሶማሌ እና በአፋር ክልሎች መካከል የይገባኛል ጥያቄ በተነሳባቸው 8 ቀበሌዎች ሊከፈቱ የነበሩ 30 የምርጫ ጣቢያዎች እንዳይቋቋሙ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሰረት በአካባቢው የሚኖሩ መራጮች ፣ ምዝገባ እና የድምጽ መስጠት ሂደትቱን በአቅራቢያቸው ባለ ሌላ ቀበሌ መመዝገብ እና ድምጻቸውን መስጠት እንደሚችሉ የገለጸው ቦርዱ ይህ ተግባራዊ እንዲሆንም ለምርጫ አስፈጻሚዎች መመሪያ እንደሚተላለፍ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡

አውሎ ሚድያ መጋቢት 15/ 2013 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com/category/zena/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ