በአክሱም ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟዋል – ኢሰመኮ

0
510

በኤርትራ ወታደሮች በአክሱም ከተማ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈፀሙን ኢሰመኮ ይፋ አደረገ፡፡

ከዚ በፊት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሳይቀር ከ እውነት የራቀ ሪፖረት እንዲሁም ውንጀላ ነው ሲሉት የነበረው የአክሱም የሰብአዊ መብት ጥሰት አውነት መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን ባወጣው ሪፖረት አረጋገጠ፡፡

የአክሱሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወይም የጦር ወንጀል ሊሆን ስለሚችል በክልሉ የተሟላ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን ኮሙሽነሩ ዳኒኤል በቀለ፡፡

በሁለት ቀናት ከአንድ መቶ በላይ ሲቪል ሰዎች በአክሱም ከተማ በነበሩ የኤርትራ ወታደሮች በተጨማሪ  የተወሰኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች  መገደላቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ፣ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መድረሱን እና በሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት አስመልክቶ መፈፀሙን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ በመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) ሪፖርቱ ይፋ አደረገ።

በሪፖርቱ ከበርካታ ሳምንታት ጥረት በኋላ የምርመራ ባለሞያዎቹን ወደ አክሱም ከተማ መላክ መቻሉን የገለጸው ኢሰመኮ፣ ባለሞያዎቹ ከየካቲት 20 እስከ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በከተማዋ በመቆየት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን፣ 45 የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የዓይን ምስክሮችን እና የሃይማኖት መሪዎችን ማነጋገራቸውን አስታውቋል።

እንዲሁም 20 ሰዎች የተሳተፉበት የቡድን ውይይት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ማድረጉንም ነው የገለፀው። በተጨማሪም ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከአክሱም ቅድስት ማርያም ሆስፒታል፣ ከአክሱም ሪፈራል ሆስፒታል፣ ከሚመለከታቸው የቀበሌ መስተዳደር አካላት እንዲሁም ከሃይማኖት ተቋማት አገልጋዮች የተለያዩ የምስል፣ የድምጽ እና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን አመልክቷል።

ኮሚሽኑ በዚህ ምርመራው ያሰባሰባቸው መረጃዎች፣ በተለይም ከኅዳር 19 እስከ ኅዳር 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በነበሩት ሁለት ቀናት “ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደተፈጸመ” ይፋ አድርጓል። የአክሱም ከተማ እና አከባቢው ነዋሪዎች፣ ከተለያዩ የትግራይ አከባቢዎች ጦርነት ሸሽተው በከተማዋ የተጠለሉ ተፈናቃዮችና እንዲሁም የኅዳር ፅዮን ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓልን ለማክበር ከተለያየ ቦታዎች የመጡ ሰዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከአንድ መቶ በላይ ሲቪል ሰዎች በወቅቱ በአክሱም ከተማ በነበሩ የኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል። በዚህ የቀዳሚ (መጀመሪያ ደረጃ) ሪፖርት የተጠቀሱ አኃዞች አጠቃላይ የተጎጂዎችን ቁጥር እንደማያመለክቱ የገለፀው ኮሚሽኑ ይህ ሪፖርት “እስከዚህ ምርመራና ሪፖርት ወቅት ድረስ ብቻ ለማረጋገጥ የቻለውን የሲቪል ሰዎች ጉዳት የሚጠቁም ነው” ብሏል። በቀዳሚ ሪፖርቱ እንደተገለፀው፣ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ፣ የተጎጂ ቤተሰቦች እና የአይን እማኞች በርካታ ሲቪል ሰዎች ልጆቻቸው፣ ሚስቶቻቸው እና እናቶቻቸው ፊት ጭምር በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉ አስረድተዋል። 

ይህ በወቅቱ “በአክሱም ከተማ በነበሩት የኤርትራ ወታደሮች የተፈጸመው መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተራ ወንጀል ሳይሆን በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና መርኆች የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የሚጥስ፣ በግጭቱ ተሳታፊ ያልነበሩ ሲቪል ሰዎች ላይ ጭምር ሆነ ተብሎ ያነጣጠረ እና በሚሊተሪ አስፈላጊነት ሊገመገሙ የማይችሉ እና ሆነ ተብሎ የተደረጉ በሲቪል ሰዎች ንብረቶች፣ በሃይማኖት ተቋማትና በሆስፒታሎች ጭምር ዝርፊያና ጉዳት ያደረሰ” እንደሆነም ነው የተብራራው። በመሆኑም “የሰብአዊ መብቶች ጥሰቱ ምናልባት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ወይም የጦር ወንጀል ሊሆን ስለሚችል፤ በአጠቃላይ በክልሉ የተሟላ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ምርመራ ስራ ማካሄድ ያስፈልጋል” ብሏል ኮሚሽኑ። 

የሰዓት እላፊ ገደብን ለማስከበርና በደኅንነት አጠባበቅ ምክንያት በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች የሚወሰደው እርምጃ “ለሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉድለት መድረስ ምክንያት መሆኑ እጅግ አሳሳቢ መሆኑንም” ሪፖርቲ ጠቅሷል። የሰዓት እላፊ ገደብን ተላልፎ የተገኘ ሰውንም ቢሆን በተመጣጣኝ ኃይል በቁጥጥር ስር ማዋል ስለሚቻል፤ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል በመጠቀም የተወሰዱት እርምጃዎችና በዚህ መልክ የተገደሉ ሰዎች ሁኔታ በተሟላው ሪፖርት የጸጥታ ኃይሉንም ምላሽ በማካተት የሚጣራ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በሲቪል ነዋሪዎች ደኅንነት አጠባበቅ ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል አጠቃቀም በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባ ሪፖርቱ ያመለክታል። 

“በትግራይ ክልል የተከሰተውን አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በአለም ዓቀፉ የሰብአዊ መብቶች ድርጅትና በኮሚሽኑ የጣምራ ምርመራ ቡድን (joint investigation team) አማካኝነት እንዲጣራ የፌዴራሉ መንግስት ስምምነቱን ማሳወቁ ትክክለኛ እርምጃ ነው” ብለዋል የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ። አክለውም “አብዛኛው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባሎች በሕይወት መስዋእትነት ጭምር አገራቸውንና ሕዝብን የሚያገለግሉ ቢሆንም፣ በተወሰኑ የሠራዊቱ አባሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ለጣምራ ምርመራ ቡድኑ (joint investigation team) የሰብአዊ መብቶች ምርመራ ስራ ተገቢውን እገዛ ማድረግ ይገባል” ብለዋል።

የኤርትራ ወታደር ድንበር ጥሶ በኛ ህዝብ ላይ የሚያደረገው ጥፋት በማነኛውም መንገድ አንቀበልም ፤ ይህን የማንቀበለው የኤርትራ ወታደር ስለሆነ ሳይሆን የኢትዮጵያም ጭምር ቢያርገው ተቀባይነት የለውም ፡፡  ዘመቻው በግልፅ ከተለዩ ጠላቶች እንጂ ከህዝብ ጋር አይደለም ፤ በማንኛውም ሰዓት የኤርትራ ወታደር በህዝብ ላይ የመብት ጥሰት ከፈፅሙ የኤርትራ መንግሰት እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትላንት ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጋር በነበራቸው ቆየታ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

አወሎ ሚድያ መጋቢት 15/2013 ዓ/ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ቴሌግራም፦ https://t.me/awlomedia
ትዊተር፦ https://twitter.com/AwloMedia

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/channel/UCFRuICCV8fHJGa3AbcA3zOA
ድረ ገጽ፦ https://awlomediatv.com/category/zena/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/awlomedia

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ