የአውሮፓ ሕብረት በኤርትራው ብሔራዊ ደኅንነት ተቋም ላይ ማዕቀብ ጣለ

0
337

ሕብረቱ ማዕቀብ ለመጣል የወሰነው የደኅንት መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል በሚል ነው። ይህም የዘፈቀደ ግድያ፣ እንግልት፣ እስር እና የሰዎች መሰወርን ይጨምራል።

ይህንንም ተከትሎ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ የሕብረቱን ውሳኔን “ጥቃት እና ውጤት የማያስገኝ” እርምጃ እንደሆነ በመግለጽ እንደማይቀበለው ገልጿል።

ጨምሮም ሕብረቱ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ሕጋዊም ሆነ የሞራል የበላይነት የለውም በማለት “ለሌላ ድብቅ አላማ ሲባል ኤርትራን ለማሸማቀቅ በሐሰት የተቀነባበረ ክስ ነው” ሲል አጣጥሎታል።

የአውሮፓ ሕብረት ምን አይነት ማዕቀብ አንደጣለና ማዕቀቡን በዚህ ወቅት ለምን መጣል እንዳስፈለገ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው አውሮፓ ውስጥ የኤርትራ ብሔራዊ ደኅንነት መስሪያ ቤት ንብረቶች ይታገዳሉ።

ይህ ቢሮ የሚመራው በሜጀር ጀነራል አብርሃ ካሳ ሲሆን፤ ተጠሪነቱም ለአገሪቱ የፕሬዝዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጽህፈት ቤት ነው።

የአውሮፓ ሕብረት ከኤርትራ በተጨማሪ በቻይና፣ በሊቢያ፣ በሩሲያ፣ በደቡብ ሱዳን እና በሰሜን ኮርያ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚያሳስቡት አስታውቋል።

በሕብረቱ የተጣለው ማዕቀብ 11 ሰዎችና አራት ተቋማትን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።

የአውሮፓ ሕብረት ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና የመብት ጥሰት የፈጸሙ ተጠያቂ እንዲሆኑ በማሰብ ማዕቀቡን መጣሉ ተዘግቧል።

በኤርትራ እና በደቡብ ሱዳን የዘፈቀደ ግድያ እንዲሁም በሩሲያ የፓለቲካ ተቃዋሚዎች የሚደርስባቸውን እንግልት ሕብረቱ አውግዟል።

በቻይና፣ በሊቢያ እና በሰሜን ኮርያ የዘፈቀደ ግድያ፣ የሰዎች መሰወር እና ስቃይንም ኮንኗል።

በአውሮፓ ሕብረት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በሚመለከት ማዕቀብ የሚጥለው አካል ያስተላለፈው ውሳኔ ወደ አውሮፓ የሚካሄድ የጉዞ እገዳን ይጨምራል።

የአውሮፓ ሕብረት አባላት ማዕቀብ ለተጣለባቸው አካላት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የገንዘብ ድጋፍ እንዳያደርጉም ዕገዳ እንደተጣለባቸው ተገልጿል።

ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው የአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ክንፍ የተቋቋመው አምና ጥቅምት ወር ላይ ነበር።

ኤርትራ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የመብት ድርጅቶች በሰብአዊ መብቶች ጥሰትና በግድጃ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ምክንያት በተደጋጋሚ ወቀሳ ሲሰነዘርባት እንደቆች ይታወቃል ሲል ቢቢሲ ዘግበዋል።

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ