በ እነ አቶ ስብሃት ነጋ ጉዳይ ይደመጣል ተብሎ የነበረው የቅድመ ምርመራ ምስክር ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

0
220

ችሎቱ ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠው የእነ ስብሃት ነጋ ጠበቆች ማረሚያ ቤት ሄደን መግባት አልቻልንም ከፍርድቤት ጥብቅና ፍቃዳችሁን አቅርቡ ብለውን ተመልሰናል ባልተመካከርንበት ሁኔታ ምስክር መሰማቱ ተገቢ ስላልሆነ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን በማለታቸው ነው፡፡

ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት ያቀረበው የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ሲሆን ተጠርጣሪዎቹ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነው የቀረቡት፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ችሎት የቀረቡት የዐቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ ምስክርን ለመስማት በተሰጠ ተለዋጭ ቀጠሮ ነው፡፡  ዐቃቤ ህግ ባሳለፍነው ሳምንት 50 ምስክሮች ማዘጋጀቱን መግለጹን ይታወሳል፡፡


አምባሳደር አባይ ወልዱ አይናቸው እየተጋረደ ስለሆነ በግል እንዲታከሙ ይታዘዝ፤ አቶ ስብሃት በግል እንዲታከሙ የታዘዘው ትዕዛዝ ተፈጻሚ አልሆነም የሚል አቤቱታ አሰምተዋል፡፡

ተጠርጣራዎቹ ከቤተሰብ ምግብ ቅዳሜና እሁድ ብቻ እንደሚገባላቸው በመጥቀስ፥ ከሰኞ እስከ አርብ እንዲፈቀድ ትዕዛዝ ይሰጥልንም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የተጠርጣሪዎቹ ቁጥር ብዙ መሆኑን በመጥቀስም እድሜያቸው የገፉና ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው ስላሉ ለኮሮና እንዳይጋለጡ ታሳቢ ቢደረግ ሲሉም አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

ዐቃቤ ህግም የተነሱ አቤቱታዎች ተገቢነት የሌላቸውና ጠበቆችም ባለፈው ሳምንት ተጠርጣሪዎችን ማግኘት ይችሉ ነበር በማለት ጉዳዩ በጠበቆቹ ቸልተኝነት የመጣ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ይህ የቅድመ ምርመራ ምስክር በመሆኑም በአፋጣኝ ማስረጃ ለማቆየት ምስክር መሰማት እንዳለበት በመጥቀስ፥ በጠበቆች የተነሳው አቤቱታ ጉዳዩን ለማዘግየት በማሰብ ነው በሚል አቤቱታውን ተቃውሟል፡፡

ጉዳዩን የተከታተለው ችሎቱ ጠበቆቹ ስነምግባር በጎደለው እና የችሎቱን ክብር ባልጠበቀ መልኩ ተከራክራችኋል በሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡

በተነሱ አቤቱታዎች ላይ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት በይደር ለነገ ማለት መጋቢት 14/2013 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ