የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሰባት ባህሪያት

0
737

መንደርደሪያ

ባለፉት ጊዚያት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) አመለካክትን፤ ባህሪይን፤ የህይወት ውጣ ውረድንና አጠቃላይ ስኬትና ጉድለት የሚተርኩና የሚነግሩ፣ አለፍ ሲሉም የሚተቹ አስተያየቶች በተለያዩ መንገድ ተስተናግደው አስተውለናል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከግላዊ ባህሪያቸው በዘለለ የመሪነትና ፖለቲካዊ ባህሪያቸው ምን ይመስላል የሚለውን ግን ለመትለምና ለማሳየት የሞከሩ ጥቂቶች ናቸው።

የሰዎችን ባህሪይ የሚያጠኑ፣ የሚተነትኑና የሚያስረዱ ብዙ የሳይንስ ማስረጃዎችና አመንክዮዎች አሉ። ዘርፉ በአለም የሰው ልጅን ባህሪይ ከተወለደበት ወቅት፤ ከአስተዳድጉና እስከ ሰባት አመት ድረስ ባለው ባህሪይ፤ በተነገረው ትርክትና ትልም ላይ መሰረት አደርጎ የሚያስዳ ይሁን እንጅ በተጨባጭ ሰዎች የሚያሳዩት ባህርይን መነሻ በማድረግ ይህንን ይመስላል ሲል የሚያስረዳ የባህሪይ  መተርጎሚያና ትንታኔም ይሰጣል። 

ባለፉት ሁለት አመታትና ከዚያ በላይ  በሚባሉት ጊዚያት ጠ/ሚ አብይ አህመድ ያሳዩዋቸውን ባህሪያት፤ ያደረጓቸውን ንግግሮችና የተገበሯቸውን ተግባራት መነሻ አድርገን የጠ/ሚ አብይ ሰባት ልዩ ባህሪያት ብቻ በመቀንበብ ከእነ ምሳሊያዊ አስረጂዎች እንጥቀስ።

  1. ማቅለል

ነገሮችን ማቅለል የመጀመሪያው የጠ/ሚ አብይ ባህሪይ ሆኖ ይቀመጣል። በዶክተር አብይ አንደበት ይህ የሚከብደንና ሊሳካልን የማይችል ነው፤ ጥረት ይጠይቃል ፤  ወይም ደግሞ ለጊዜው ማድረግ አልችልም ፤ እናስብበት  ፤ እናቅድ የሚሉ ቃላትን ሀረጋትን ከአንደበታቸው ሲያወጡም ሆነ  ሲናገሩ አይታዩም።

በተቃራኒው የተስፋ ዳቦ የሚጋግሩ፣ ሁሉን ማድረግ የሚችሉ ሆነው ይታያሉ። ለምሳሌ በተመረጡ ሰሞን ሁሉንም ማድረግና ማስተካከል እንደሚችሉ፣ ምለው፣ ተገዝተው፣ ሁሉንም አስጨብጭበዋል። እጅግ የተስማማች ኢትዮጵያን ፤ፍትሃዊ የሆነች ኢትዮጵያን፤ ዴሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ፤ ቅሬታዎችን ሁሉ የምትፈታ ኢትዮዮጵያን መገንባት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ይህንን ማድረግ የሚቻልባቸውን መንገዶችና እቅዶችን ግን ማቅረብ አልቻሉም። ያቀረቧቸው የማቅለያም ሆነ የመፍትሔ ሀሳቦችና መንገዶች አዲስ ችግር የፈጠሩ ወይም የነበረውን ችግር የሚያባብሱ ሆነው ታይተዋል ይላሉ ብዙዎች።

‘’ተስፋ ሳንቆርጥ ሪቫን እንቆርጣለን’’ የሚል ተደጋጋሚ ንግግር ያደረጉት ጠ/ሚ አብይ ሁሉንም ለማድረግ የተዘጋጁና አቅልለው የሚያዩ መሪ መሆናቸውን ብዙዎቹ ናቸው የሚስማሙት። የዜጎች ሞትንና ብሔራዊ ጥቅምን እጅግ ቀለል አደርገው ሲመለከቱም አስተውለናል። በአንድ ወቅት የሞቱ ዜጎችን ቁጥር ሲጠቅሱ በብሔር መጥቀሳቸው የሚታወስ ነው። ‘’የምትን እኛ ያለነው እኛ’’ በማለት ሞትን አቅልለው አቅርበዋል፤ መደንገጥ፣ ማዘንና መቆጨት ያልፈለጉ ሆነው ታይተዋል። 

በጠ/ሚ አብይ አህመድ አመለካከት ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ያለ አይመስልም። ቢኖርም አይታያቸውም። ሁልጊዜ መልካም ነገር ብቻ ነው የሚታያቸው ይሏቸዋል ፖለቲካዊ ባህሪያቸውን የሚገልፁ የተለያዩ ሰዎች። በባለፈው መስከረም መጀመሪያ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ተከስቶ በርካታ ዜጎች ሲፈናቀሉና ጉዳት ሲደርስባቸው እሳቸው፣ ግን በተለያዩ የልማት ቦታዎች እየተንሸራሸሩ ከመታየታቸው ባለፈም ለጎረቤት ሀገር ሱዳን የጎርፍ ጉዳት አዝነው መፃፋቸው አስገራሚ ሆኖ ነበር። ሁሉንም ነገር ቀለል አደርገው ከማየት ባለፈ ችግርን ማየት የማይፈልጉ፣ ስለ ችግርም ማውራት የማይወዱ ፍስሃና ደስታ አብዝተው የሚወዱ፤ ‘’ስኬታማ ነን’’ ማለትን የሚወዱ ከመሆናቸው ባለፈ ሁሉንም ለማድረግ የሚያስችልና ሀይል  ያላቸው መስለው መታየት ይወዳሉ።

2. ማስመሰል

ማስመሰል የብዙ ሰዎች ባህሪይ ሲሆን፣ በመሪዎች ዘንድ ሲከሰት ግን እጅግ አደገኛ ነው። ይህም ማስመሰልና አደጋው በዓለም በተለያዩ ጊዚያት በተለያዩ መሪዎች ታይቷል። ዶክተር አብይ አህመድ አስመሰለው ከሚታዮባቸው ጉዳዮች አንዱ ህጋዊና ህግ አክባሪ መስለው መታየታቸው ነው።

ነግር ግን እንኳን ህግና  ህገመንግስትን ሊያከብሩ ቀርቶ ቀላሉን የመሪዎች የፕሮቶኮል ህግ እንኳን ሲያከብሩ አይስተዋሉም በማለት ይተቿቸዋል። በአስመራ የቡና ቁርስ ሲያቀርቡ ታይተዋል፣ ለፕሬዚዳንቱ  ኢሳያስ ቀለበት ሲያጠልቁ ታይተዋል፣ በተደጋጋሚ መሪዎችን እራሳቸው መኪና እያሸከረክሩ ሲያስጎበኙ ተመልክተናል በማለት ነው ህግ አክባሪ ስብዕና የላቸውም የሚሏቸው። ከዚህም አልፎ ፓርክ ሲያስጎበኙና ገለፃ ሲያደርጉ አይተናልና ይህም የመሪ ግዴታ አይደለም፣ በህግ አግባብም ተገቢ አይደለም የሚሉ ገጥመውናል። ነገር ግን እኔ የቀበሌ መሪ አይደለሁም በማለት ከህዝብ አጀንዳዎች ሲሸሹም ተሰምተዋል።

በሌላ በኩል ለማስደሰትና ጊዚያዊ ተቀባይነት ለማገናኘት በሚል ከፍተኛ የማስመሰል ስራ ሲሰሩ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ‘’ኢህአዴግና አሸባሪ ነበር’’፣ የዓለም የገንዘብ ተቋሙ አይ ኤም ኤፍ ‘’የእናት መቀነት ነው’’፣  ‘’የስኳር ፕሮጀክቶች በስድስት ወር ያልቃሉ’’፣’’ ሀገራዊ መግባባት አመጣለሁ’’፣ ‘’25ሺ ሾፌሮችን ወደ ዱባይ አንልካለን’’፣ ‘’ሆደ ሰፊና ዴሞክራሲያዊ ነን’’፣ ‘’ከአቶ ለማ ጋር ታርቀናል’’፣  ወ.ዘ.ተ. የሚሉ የማስመሰያ ንግግሮችን በየጊዜው ተናግረዋል በማለት ነው አስመሳይ ናቸው በማለት የሚተቿቸው።

ዶክተር አብይ አህመድ መሪ መስለውና ፖለቲከኛ መስለው መታየት ይፈልጋሉ የሚሏቸውም አልታጡም። በእርግጥ መሪ ሆነው በአለም አቀፍ ደረጃ የተሸለሙና እውቅና ያገኙ ቢሆኑም፣ በሀገር ውስጥ ያለውን ሁኔታ በምንመለከትበት ጊዜ ግን መሪ ያለው፣ ፖለቲካ የሚያውቅ መሪ የሚመራው ሀገር መሆኑን ያጠራጥራል ።

ለሀገራዊ መግባባት ብለው በሚያደርጉት የፓርቲዎች ውይይት ላይ መድረክ ላይ ሆነው፣ ከፖለቲካ ውጪ የሆነ ሰባካ ሲያደርጉ የተመለከቷቸው ብዙዎቹ ፖለቲካ አያውቁም ይሏቸዋል። ዜጎች ‘’መሪያችን የት አሉ’’፣ ‘’ይድረሱልን’’ በሚሉበት የችግር ወቅት ጠ/ሚ አብይ ድምፃቸውን አጥፍተው ለቀናት ይጠፋሉ ተብለው ይተቻሉ። ያ ካልሆነም ሌላ አጀንዳ ይዘው በመምጣት የነበረውን እንዳልነበር ለማስመሰል ይሞክራሉ። ማስመሰል ብቻ ሳይሆን ሙሉ ስራን በማስመሰል ውስጥ ማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትራችን ባህሪይ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል የሚሉ ጥቂት አይደሉም።

  1. ጀብደኝነት

ጀብደኝነት የጠ/ሚ አበይ አህመድ ሶስተኛ መለያ ባህሪይ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል። በአንድ በኩል የሚያስቡት ትልልቅ ጉዳዮችን ብቻ እንደሆነ ለማሳየት የሚጥሩት እኒህ ጠቅላይ ሚኒስትር ድንገተኛ ነገሮችን በማከናወን እና ኢ-ተጠባቂ በመሆን ማስደነቅ (ሰርፕራይዝ ማድረግ) የሚወዱ ናቸው ይባላሉ።

በመጀመሪያ የሹመታቸው ወራቶች እጅግ ቅብዝብዝ ሆነው ነበር። በሁሉም ቦታ በድንገት በመገኘት በርካታ ድንገቴ ደስታዎችን ፈጥረዋል፤ ድንገቴ ንግግሮችን አድርገዋል። የጀብደኝነት ባህሪቸው እጅጉን ጎልቶ የታየባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። ምሳሌ እንጥቀስ ከተባለ ድንገት የብር ኖት እንደተቀየረ፣ እሳቸው በቀጥታ የሚመለከታቸው ባይሆንም ብዙ ጊዜ በፌስቡክ ገፃቸው እንደ ሚያሰፍሩት፣ በየቀኑ አዲስ ተስፋ አለን የሚለውን ለማሳየት ይመስላል ከብሔራዊ ባንክ ሁሉ ቀድመው የብር ኖት ለጥፈው ታይተዋል።

በየጎዳናው መኪና ሲያሽከርክሩ መታየት፣ በየ ክልሉ ድንገተኛ ጉብኝት ማድረግ፣ የሆነ የመንግስትና የግል መስሪያ ቤትን ድንገት መጎብኘት፣ ድንገት ወደ ሌላ ሀገር ለጉብኝነት መውጣት እና ጀብድ የተሞላበት ንግግር ማድረግ ያዘወትራሉ።  በተለይ በንግግራቸው እጅግ ጀብደኛ ሆነው ለመታየት ይሞክራሉም ይታያሉም። ስለ ጀብደኝነት ተገቢ አለመሆን እርካብና መንበር በሚለው መፅሐፋቸው እንበሳን ምሳሌ በማድረግ ቢፅፉም፣ እሳቸው ግን ጀብደኛ ሆነው መታየት አላቆሙም ተብለው ይወረፋሉ።

በእነዚህ የጀብደኝነት ባህሪያቸው መከሰቻዎች ላይ ባደረጓቸው ንግግሮች በፈፀሟቸው ተግባራት እጅግ ብዙ ዜጎች አስቀይመዋል ተብለው ይከሰሳሉ። በተጨማሪም ማስጨብጨብና መሞገስ የሚወዱ በመሆናቸው  እጅግ የከፉና ተገቢነት የሌላቸውን ንግግሮች በማድረግ በልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እና የፖለቲካ ሃይሎች ጥርስ ውስጥ ገብተዋል።

ጀብደኝነታቸውን የሚጀምሩት ‘’ልገደል ነበር’’፣ ‘’እጅግ የከፋ ትግል አድርጌ ነው ስልጣን የያዝሁት’’ ከሚል ነው። ዘወር ብለው ደግሞ በህዝብ ትግል ስልጣን እንደያዙ ሲናገሩ ይሰማል። ጠ/ሚ አብይ በግላቸው የማያምኑባቸውን በርካታ ታሪኮችና የታሪክ ሰዎች ለህዝብ ጭብጨባ ሲሉ አሞካሽተዋል፤ በተቃራኒው ተችተዋል።

‘’እኛ ገድላችሁ ነው ኢትዮጵያን የምታፈርሷት’’ የሚለው ንግግራቸው እጅግ ጀብድ የተሞላበት ለኢትዮጵያ ብቸኛ የብረት መዝጊያ እንደሆኑ ለማሳየት የሞከሩበት አንዱ ነው።

በአንድ ወቅት ድንገቴነትና ጀብደኝነት ከመውደዳቸው የተነሳ በርካታ ዜጎች ድንገት ቤታቸው ተከስተው አብረዋቸው እራት ወይም ምሳ ሊበሉ እንደሚችሉ  ያስቡ እንደነበር በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ብዙዎቹ ፅፈዋል። በተለይ ደግሞ ወደ አስመራ በልቡ ሙሉነት በመሔድ እንታረቅ ማለታቸው ከመልካም ጀብደኝነታቸው ውስጥ ቀዳሚ ተጠቃሽ ሆኖላቸዋል።

4. የድል አጥቢያ ጀግና

ይህ ከፍተኛ ትግልናና ከፍተኛ ስራ ሲራበት በኖረ በአንድ ክተት ወይም በአንድ ፕሮጀክት ላይ ወደ መጨረሻው መጥቶ   ሲያልቅ ቀዳሚ ሰሪ ነበርኩ ብሎ ንግግር ቢያደርግ ወይም ቢሸለም ወይም ስለ ስራው ታሪክ ላውራ ቢል በተለምዶ የድለ አጥቢያ  ጀግና ይባላል።

ለምሳሌ የኢንዱስትሪ ፓርኮችንም ሆነ ሌሎች ቀድመው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ሲመርቁ ከእሳቸው በፊት ያለው መንግስት የጀመራጀው መሆናቸውን በመካድ በእሳቸው መሪነት የተሳኩ አድርገው ያቀርባሉ። ቀደም ሲል በሀገር ደረጃ ተይዘው የነበሩ ፕሮጀክቶችንም እሳቸው የጀመሯቸውና ያቀዷቸው ለማስመሰል ይጣጣራሉ በማለት ይተቿቸዋል። የምኒሊክ ቤተመንግስት እድሳትና እና የእንጦጦ ፓርክ ፕሮጀክት ቀደም ሲል በእቅድ ተይዘው የነበሩ ቢሆን ያለ ሀፍረት ሙሉ ሀሳቡን ያመነጨሁት እኔ ነኝ ሲሉ ተደምጠዋል ።

በሌላ በኩል በበርካታ ጉዳዮች ላይ የተጀመሩ ስራዎችን እና ነባር ፕሮጀክቶችን ለስማቸው ትልቅነት ሊጠቀሙባቸው ሞክረዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አንዱ ነው። የነበረውን ስራ እጅግ ካጣጣሉና ‘’አይረባም፣ በአስር አመትም አያልቅም’’ ካሉ በሗላ መልሰው ‘’በሁለት ዓመት ያልቃል፣ ይህንንም ያደረግሁት እኔ ነኝ’’ ሲሉ መደመጣቸው ብዙዎችን አስገርሞ ነበትር።

እነዚህና ሌሎች ያልተጠቁሱ ጉዳዮች ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን የድል አጥቢያ አርበኛ ሊያስብሏቸው ይችላሉ።

5. ሀይማኖተኛ መምሰል

የኢትዮጵያ አስትሮሎጂ ወይም ፍትሃ-ነገስት እንደሚያስረዳው ከሐምሌ 13 እስከ ነሐሴ 12 የሚወለዱ ሰዎች ባህሪይ “አሰድ” በመባል የተሰየመ ሲሆን ሙሉ ባህሪያቸው ከአንበሳ ጋር የተመሳሰለ ትርጓሜ ተሰጥቷል።

ታዲያ እነዚህ በአሰድ ስር የተሰየሙት ባህሪያት ያላቸው ሰዎች መገለጫቸው አንዱ ሀይማኖተኛ መስሎ መታየት እና ለሁሉም ተወዳጅ ለመሆን መሞከር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይህ ባህሪይ በደንብና በግልፅ ይታይባቸዋል። በተለየም እጅግ ሀይማኖተኛ መስለው የሚታዩ ከመሆናቸው ባለፈ ከሀይማኖትና ከእምነት በማጣቀስ ንግግር ማድረግ፣ መፃፍና ማውራትም ይወዳሉ።  በተለይም በክርስትና እና በእስልምና እምነት ውስጥ  ከፍተኛ መስተጋብር ሲፈጥሩ ይሰተዋላል።

መንግስትና ሀይማኖት ለየቅል ናቸው ቢባልም ለመንግስታቸው መፅናት ለዜጎች ፀልዩ ሲሉ ይደመጣሉ። ‘’የሚያኖረኝ የእናቶች ፀሎት ነው’’፣ ‘’ከኖቤል ሽልማት ሁሉ የበለጠው ሽልማት የእናት ምርቃት ነው’’ ሲሉ ተደምጠዋል። ዲራአዝ በሚል የብእር ስም ባሰተሙትና ከሹመታቸው በሗላ በአንድ መድረክ ላይ እንደተናገሩት እርካብና መንበር የሚል መጽሐፋቸው ወስጥ ይህ ባህሪያቸው በዝብርቅርቅነት ተስተውሏል።

በዚህ መጽሐፍ መግቢያ ላይ እናታቸው ወይዘሮ ትዝታና ባለቤታቸው ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ላደረጉላቸው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል። በሌላ በኩል ለእናትና ለሀይማኖት የተለየ ክብር ያላቸው መሆኑን በተለያዩ ሁኔታ አስረድተዊል። እናቶች እንዳያለቅሱ፣ አባቶች እዳያዝኑ ሲሉ ይናገራሉ። ዶክተር አብይ በአንዳንዶቹ ሁሉም ሀይማኖት ላይ በሚያሳዩት የእኔነትና የአለሁበት እንቅስቃሴ የተነሳ  “ፈሪሃ እግዚአብሔር” የሚያውቁ ናቸው ተብለው ተገልፀዋል።

ነገር ግን   ለሀይማኖት ልዩ ትኩረት አለኝ የሚሉት እኒሁ ጠቅላይ ሚኒስትር በፀጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ቤተ እምነቶች ሲፈርሱ፣ ሲቃጠሉ፣ አማኒያን ሲሞቱና ሲሰደዱ ዝም ማለታቸው ከመምሰል የዘለለ ሀይማኖተኛነት እንደላቸው ለማመን አጠራጣሪ ሆኖ ይታያል  የሚሏቸው ብዙ ናቸው።

በየ በዓላቱ፣  በአውደ አመቱ የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች እና በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ሁሉ ለሀይማኖት ቅርብ የሆኑና በሀይማኖታቸው ምክንያት ተቀባይነት ያላቸው ሰዎችን መሆናቸው ሀይማኖተኛ መስለው እንዲታዩ የሚደረግ ጥረት  የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባህሪይ መሆኑን ይገለፃል።

6. እኔ ባይነት

በቅርብ ጊዜ ‘’እንደኔ በዓለም ስኬታማ መሪ የለም’’ ሲሉ ተናግረው ነበር ጠ/ሚ አብይ። ‘’እኔ’’ ማለት መደበኛ ቋንቋቸው ነው። አንዳንድ የስነ ልቦና ባለሙያዎች በእናታቸው የተነገራቸው የሰባተኛ ንጉስነት መገለጫ አድርገው ያቀርቡታል። 

‘’የእኔን ጥሪ ተከትሎ ዜጎች ወጥተው አምስት ቢሊዮን ችግኝ ተከሉ፣ ስለዚህ ደጋፊ አለኝ’’ ሲሉ መናገራቸው የተጣባቸው ፖለቲካዊና ስነ ልቦናዊ ባህሪይ ነው ተብሎላቸዋል።  በተለያዩ ሁኔታዎች፣ ክስተቶችና መድረኮች እኔ የሚለውን ንግግራቸው ከማዘውተራቸውም በላይ ተቀባይነት እንዲያገኙ ሲጥሩ ይስተዋላሉ።  ‘’እኔ አቅጄ ፣እኔ አስቤ ፣እኔ ወስኘ፣ እኔ መርቼ ፣ . . .  አሻግራችኃለሁ’’ በማለት ይናገራሉ።

 አንዳንዴም  ‘’እኔ እያለሁ፣ አኛ አያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም’’ ሲሉም ይደመጣሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር  አብይ አህመድ እኔ ይበሉ እንጂ መንግስቴ ወይም መንግስታችን ብልፅግና ሲሉ አለመደመጣቸው ደግሞ ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል።  የተለያዩ ሹመቶችን ሰጡ፣ የየከሌ ክልል ካቢኒን መልቀቂያ አስገቡ አሏቸው፣ እነ የከሌ በጠ/ሚ አብይ እውቅና ተሰጣቸው . . . የሚሉ ዜናዎች ሰርክ የምንሰማቸው ናቸው። 

ለምሳሌ በአድነትና በእጦጦ ፓርኮች በስራ አስኪያጅነት ሰማቸው መስፈሩ እና ‘’በእኔ ሀሳብ አፍላቂነት ነው የተሰራው’’ ማለታቸው አስገራሚ ነው የሚሏቸው አሉ። በእርግጥ ዶክተር አብይ በጋራ ስለመሆን ፣አብሮ ሰለመስራት፣ አብሮነትና ወንድማማችነት የሚጠናክሩ ቃላትና ሀሳቦችን ቢያበዙም መደመር ያሻግራል ፣ ብቸኛ መንገዳችን መደመር ነው ቢሉም ፣እኔ ከማለት ግን  አልተቆጠቡም። መደመር ሌላውን በማቅለጥ ወደ እኔነት የሚወስድ መንገድ ይሆን እንዴ በማለት የጠረጠሩም ብዙ ናቸው።

በሁሉም ዘርፍና ሙያ ላይ የማሻሻያ ሀሳብ ሲያቀርቡ፣ ሲተቹ እና እንዲህ ይደረግ ሲሉ መታየታቸውም ሌላው የእኔ ባይነት ፖለቲካዊ ባህሪያቸው መገለጫ ሆኖ ተመዝግቦላቸዋል።

7. ራስን መውደድ

እዚህ ላይ ናርሲዝም የተሰኘ የስነ-ልቦና ውቅር መገለጫ እንመልከት። ናርሲዝም አፍቅሮተ እራስ ሊባል ይችላል። በግሪክ ራሱ አብዝቶ የሚወድ እንድ ሰው መነሻ በማድረግ የተፈጠረ ሳይንስ ነው። ግሪካዊው እራሱን አብዝቶ በመውደዱ የተነሳ መስታዎት ፊት ቆሞ ውበቱን ሲያደንቅ ይውል ነበር። መስታወት ማየት ሲከለከል ወንዝ ዳር ሔዶ እራሱን ውሓ ላይ እያየ ነው ያረፈው። ነገሩ ከውልደት ሂደቱ ጀምሮ የተነገረው ትርክት ያመጣበት ጣጣ ነው። አንተ ከመላዕክት የተገኘህ ነህ፣ ከሰው ትለያለህ ተብሏል። ውብና ቆንጆ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የተለየህ ነህ ተብሎ ስለተነገረው እራሱን አፈቀረ ይላል የግሪክ ሀተታ ተፈጥሮ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለፎቶ ፣ ለራስ ምስል ለአጠቃላይ እኔ ባይነትን  ያጋለጣቸው ጉዳይ በልጅነታቸው ንጉስ ነህ መባላቸው እንደሆነ ይነገራል። እራሳቸውም እንኳን አሁን ተማሪ እያሉም ንጉስ  እንደነበሩ፣ ጓደኞቻቸውም ንጉሰ እንደሆኑ ያምኑ እንደነበር ተናገረዋል በማለት ማስረጃ ይጠቀስባቸዋል። ከዚህም ተያያዘ ከሌላ የራስን ምስልና የራስን ስም ብቻ መውድድ፣ ስለ እሱና እሱ ብቻ እንዲወራ መፈለግ ግን የጠ/ሚ አብይ ልዩ ባህሪይ ነው የሚሉ ብዙ ናቸው።

በአጠቃላይ ዘርዝረን ያየናቸው ሰባት  የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ባህሪያት ከሚያደርጓቸው ተግባራት፣ ንግግሮችና ፍላጎት ተነስተን ልንላቸው የምንችል እንጂ በድፍረት ሳይንሳዊ ትንታኔዎች ፣ የላባራቶሪ ውጤቶች ናቸው ለማለት አይደለም። የመሪዎቻችን ባህሪ ለማወቅ የሚረዳ ውይይት ይከፍታሉ ከሚል የሰፈሩ መሆናቸውን አንባቢ እንዲረዳ እንፈልጋለን።

በቃሉ አላምረው

አውሎ ሚዲያ

21 ጥቅምት 2013 ዓ/ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ