በኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጎርፍ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸዋል

0
122

ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች በጎርፍ ሊጎዱ ይችላሉ የሚል ጥናት ቀርቦ ነበርም ተብሏል።

በኢትዮጵያ በተለይ በነሀሴ ወር የጣለውነ ከባድ ዝናብ ተከትሎ የመጣ ጎርፍ በተለያዩ አካባቢዎች በርካቶችን ለጉዳት ዳርገዋል፡፡በተለይ በአፋር፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተከሰተው ጎርፍ የሞትና የፈናቀል አደጋ አስከትሏል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን እንዲሁም በአፋር ክልል ሁሉም ዞኖች የተከሰቱ ዜጎች እንዲፈናቀሉና ማሳዎቻቸው በጎርፍ እንዲወሰዱ አድርጓል፡፡ ጉርፉ ነዋሪዎችን ከማፈናቀል ባሻገር እንስሶቻቸው ወስዶባቸዋል፡፡

በክረምቱ በደረሱ የጎርፍ አደጋዎች ዜጎች ለጉዳት ሲዳረጉ ሙሉ ለሙሉ መኖሪያ ቀያቸውን ለቀው እንዲፈናቀሉም አድርጓል፡፡ በተለይ ይህ በቅርቡ በአዋሽ ወንዝ አካባቢ ባሉ ነዋሪዎች ላይ ጫናው ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በክረምት ወቅት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለጉዳት ሊዳረጉ እንደሚችሉ የሚያመለክት ጥናት አቅርበው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በጎርፉ ምክንያት ለጉዳት ሊጋለጡ ይችላሉ ተብለው ከተገመቱት ሁለት ሚሊዮን 66ሺ 683 ሰዎች መካከል 434 ሺ የሚሆኑ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉም ቅድመ ግምት መቀመጡን የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

  በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቅና ምላሽ ዳይሬክተሯ ወ/ሮ አልማዝ ደምሴ እንዳሉት አሁን ላይ በርከቶች ማሳቸው በጎርፍ መበላሸቱን እንዲሁም ዜጎች ለመፈናቀል መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሰረት በአፋር ክልል 200 ሺ ሰዎች በጎርፉ ንብረታቸው መውደሙን ከ 31 ሺ በላይ የሚሆኑት ደግሞ መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል፡፡ በመተሐራና በመርቲ አካባዎችም ቢሆን በርካታ ዜጎች መፈናቀላቸውን ያነሱት ዳሬክተሯ አሁን ላይ ምግብነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ለማድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በመደበኛነት ወንዞች ከሚያደርሱት ጉዳት ባለፈ ግድቦችም ለችግሩ መከሰት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ይገልጻል፡፡ እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ ግድቦችን በሚገባ ማስተዳደርና መምራት ባለመቻሉ ውኃ ሲለቀቅ በአቅራቢያ ያሉ ዜጎች ለጉዳት እየተዳረጉ ነው ተብሏል፡፡

አሁን ላይ በጎርፍ እየተጠቁ ያሉት አፋር ክልል ሁሉም ዞኖች፣አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ፣ደቡብ ጎንደር ፣ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን፣ደቡብ ወሎ፣ ኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና በሌሎችም የክልሉ ዞኖች ፣በጋምቤላ አኙዋክና ኑዌር ዞኖች በሱማሌ ክልል ሽንሌ ዞን መሆኑ ተገልጿል፡፡

ዳይሬክተሯ ወ/ሮ አልማዝ ደምሴ በዚህ የክረምት ወቅት ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች በጎርፍ አደጋ ለጉዳት መጋለጣቸውን አስታውቀዋል፡፡ 1 ሚሊዮን 17ሺ 854 ዜጎች ለጉዳት ሲዳረጉ ከዚህ ውስጥ 292 ሺ 863 ዜጎች ደግሞ እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል፡፡

አሁን ላይ በዘላቂነት ዜጎችን ከጉዳታቸው እንዲወጡ ለማድረግና መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡ ይህም መንግስታዊ በሆኑና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት አማካኝነት እየተሰራ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ለአብነትም ማሳቸው የተወሰደባቸውን ምርጥ ዘር እንዳይቸገሩ በማድረግ፣ጤናቸው እንዲጠበቅ በማድረግና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ገንዘብ መጠንም መቀመጡን ዳይሬክተሯ አንስተዋል፡፡በአጠቃላይ ዜጎችን ከጉዳታቸው እንዲያገግሙና የተፈናቀሉትንም መልሶ ለማቋቋም 130 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈለግና ይህም በተለያዩ አካላት ትብብርን እንደሚሸፈን ተገልጿል ሲል አል ዐይን አስነብቧል።

አውሎ ሚዲያ መስከረም 02/2013 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ