የኢዜማ መግለጫ መከልከል ጉዳይ !

0
124

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አለ ስላለው “የመሬት ወረራ እና ኢፍትሃዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እደላን” በተመለከ ሊሰጥ የነበረው መግለጫ ተከለከለ።

ፓርቲ ዛሬ [አርብ] ረፋድ አምስት ሰዓት ላይ በራስ ሆቴል ሊሰጠው የነበረው መግለጫ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በፖሊስ በመከልከሉ መስተጓጎሉን የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ መግለጫው እንዲቋረጥ የተደረገው የፖርቲው አመራሮች ፈቃድ ሳይኖራቸው ስብሰባ ማድረግ ስለማይችሉ መሆኑን ገልጿል።
አቶ ናትናኤል ጋዜጣዊ መግለጫውን በተመለከተ ከዚህ ቀደም መግለጫ ሲሰጡ እንደሚያደርጉት ሁሉ ቀድመው ለሆቴሉ ማስታወቃቸውንና ለሰላም ሚኒስቴርም ደብዳቤ ማስገባታቸውን ገልፀውልናል።

ፓርቲው መግለጫውን ሊሰጥ የነበረው በአዲስ አበባ ውስጥ የሚደረግ “የመሬት ወረራን” እና “የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ እደላ”ን በተመለከተ የሚደርሱ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ ጥናት እንዲያደርግ በፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የሚመራ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት ካደረገ በኋላ፣ ውጤቱን ይፋ ለማድረግ እንደነበር አቶ ናትናኤል አስታውቀዋል።

በፖሊስ የተከለከለው የዛሬው መግለጫም የኮሚቴውን የጥናት ውጤት ለሕዝብና ለጋዜጠኞች ይፋ ለማድረግ ያለመ እንደነበር የፓርቲው የሕዝብ ግንኑነት ኃላፊ አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ መግለጫውን ለመስጠት ሆቴሉ ቦታውን አዘጋጅቶ፤ ጋዜጠኞችም በቦታው ደርሰው፤ እነርሱም በቦታው ቢገኙም በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ጋዜጣዊ መግለጫውን እንዳያደርጉ መከልከላቸውን ተናግረዋል።በዚህም ምክንያት ጋዜጣዊ መግለጫው ሳይደረግ ቀርቷል ብለዋል።

ፖሊስ የሰጣቸውን ምክንያት የጠየቅናቸው አቶ ናትናኤል፤ “መግለጫውን ማድረግ እንደምትችሉ ከበላይ አካል ትዕዛዝ ይምጣልን” የሚል መልስ እንደሰጧቸው እና የበላይ አካል ካሏቸው አካላት መካከል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የፀጥታና አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊን መጥቀሳቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ከዚህ በፊት ኢዜማ በአዲስ አበባ የሚደረግ “የመሬት ወረራ እና ኢፍትሃዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እደላ” ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማብራሪያ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ምላሽ አለማግኘቱን አቶ ናትናኤል አስታውሰዋል።

ማብራሪያ እንዲሰጠው የጠየቀው የጥናት ቡድኑ ያገኛቸውን ውጤቶች በማያያዝ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ምልከታ ለማካተት በማሰብ እንደነበር አክለዋል።
“ሪፖርቱን ከአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን፤ ከሁሉም ወገን መረጃ ሰብስቦ ማካተት ተገቢ ነው፤ በሚል እምነት በእነርሱ በኩል ያለውን መረጃ ለማካተት ነበር የጠየቅነው” ብለዋል አቶ ናትናኤል።

ደብዳቤውን ለአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት፣ ለቤቶች ልማት ኤጀንሲ እና ለመሬት ልማት ቢሮ ማስገባታቸውን ገልፀው፤ የከንቲባ ጽ/ቤት ደብዳቤውን ተቀብሎ ምላሽ አለመስጠቱን፤ ሁለቱ መሥሪያ ቤቶች ደግሞ ደብዳቤውን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ ለቢቢሲ ፓርቲው መግለጫውን እንዳይሰጥ የተከለከለው “ማሟላት የነበረበትን መስፈርት ባለማሟላቱ ” መሆኑን ተናግረዋል።

ዋና ኢንስፔክተሩ ኢትዮጵያ ያለችው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መሆኑን በማስታወስ፣ በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ስብሰባዎች መካሄድ ያለባቸው ለኮሮናቫይረስ በማያጋልጥ ሁኔታ መሆኑን ተናግረዋል።
ነገር ግን ይህንን ባላሟላ መልኩ ስብሰባዎችን ማድረግ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መጣስ በመሆኑ” ፖሊስ ስብሰባውን መከልከሉን ተናግረዋል።

አዉሎ ሚዲያ ነሀሴ 23/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ