ህወሓትና ብልፅግና ከማንኛውም የፖለቲካ ሀይል ጋር ድርድርና ውይይት እናደርጋለን ብለዋል- የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት

0
117

ከሰሞኑ ወደ ትግራይ ክልል ሔዶ የነበረው የሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ የትግራይ ክልል መንግስት የሚያስተዳድረው  ህወሓት ከማንኛውም  የፖለቲካ ሀይል ጋር ለመወያየትና ለመደራደር ዝግጁ እንደሆነ ተረድተናል በማለት የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት አስታውቋል።

የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ዛሬ በሰጠው መግለጫ በህወሓት በኩል ሁሉንም አሳታፊ በሆነ መንገድ ከማንኛውም የፖለቲካ ሀይል ጋር ውይይትና ድርድር ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑን አረጋግጫለሁ ነው ያለው።

በሌላ በኩል የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ከትግራይ ክልል መልስ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ጋር ወይይት አድርጌ ለውይይትና ለድርድር ዝግጁ ነን ብለዋል ነው ያለው። ብልፅግና ፓርት ከህወሓት ጋርም ሆነ ከሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ለሽማግሌዎቹ እና ለሀይማኖት አባቶቹ አሳውቋል ተብሏል።

የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንዳስታወቁት መማክርቱ ለህወሓትና ለብልፅግና የህዝቦች ሰላም አስፈላጊ በመሆኑ ተቀራርበው እንዲነጋገሩ ጥያቄ አቅርበን በሁሉቱም በኩል ውይይትና ድርድር አስፈላጊ መሆኑን አምነውበታል ብለዋል።

ሰብሳቢው ከዚህ በፊት በአማራ እና በትግራይ መሪዎች ፤ በኦሮሚያና በሶማሌ መሪዎች ፤ በአፋርና በሶማሌ መሪዎች መካከል የእርቅና የድርድር ስራ ተከናውኗል ያሉ ሲሆን ይህ የአሁኑ ወደ ትግራይ የተደረገው ጉዞም ቀደም ሲል ከተጀመረው የቀጠለ ነው ብለዊል።

የሽማግሌዎች መማክርት አባል አትሌት ሺ አለቃ ሀይሌ ገብረ ስላሴ በበኩሉ የእርቅና የድርድር ሀሳቡን አቅርበንላቸው ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን በማወቃችን በቀጣይ ሰላማዊ ሀገር በመገንባት ከድህነት ለመላቀቅ የምናደርገውን ጥረት የሚያግዝ ነው በሏል።

በተለይ የፖለቲከኞች ፀብና ጭቅጭቅ ለጠላት በር የሚከፍት ለርሐብና ለስደት የሚዳርግ በመሆኑ የመማክርት ጉባኤው የፖለቲካ ሀይሎች እንዲደራደሩ የሚያስችሉ ተግባራትን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያለው አትሌት ሺ አለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ።

የመማክርቱ ሌላኛው አባል ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ ከህወሓትና ከብልፅግና ውጭ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ምሁራንን ያሳተፈ ውይይትና ድርድር በቀጣይ ለማዘጋጀት የታሰበ መሆኑን ገልፀው ዜጎች ሰላማዊ ህይወት እንዲኖራቸው የፖለቲካ ሀይሎች ልዩነታቸውን በውይይት ለመፍታት መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።

የመማክርት ጉባኤው በህወሓት በኩል ከህወሓት ስራ አስፈፃሚዎች ያሉ ቅሬታዎችንና ክፍተቶችን ሙሉ በሙሉ አዳምጫለሁ ያለ ሲሆን በተመሳሳይ በብልፅግና በኩልም የሚቀርቡ ችግሮችንና ቅሬታዎችን አዳምጫለሁ ብሏል። በህወሓት በኩል የቀረበውን ቅሬታም በቀጥታ ለብልፅግና አመራሮች በማቅረብ እንዲያስቡበትና ለውይይት ዝግጁ እንዲሆኑ ጠይቀን ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀውናል ብሏል።

የመማክርት ጉባኤው በሁሉም በኩል የተበዳይነትና የተገፋሁ ቅሬታ በሰፊው ይቀርባል ይህ ደግሞ ችገሮች ከራስ ጀምሮ አለመመርመር  በመሆኑ በቀጣይ በሚደረጉ ወይይቶችና ድርድሮች የሚፈታ ይሆናል ነው የተባለው።

በቀጣይ ከሁሉም ወገን የተውጣጡ ሀይሎች ያሉበት ድርድር ለማካሔድ እየተዘጋጀን ነው ያለው መማኮርት ጉባኤው ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር በሰላማዊ መንገድ እንድትወያይ በማለት ስራውን በፈቃደኝነት እያሰፋ ነው ብሏል።

በቅርብ ጊዜ በኦሮሚያ የፖለቲካ ሀይሎች ላይ ያለውን ልዩነት በማርገብ ወደ ድርድር እንዲመጡ ለማድረግ ተመሳሳይ ስራ እሰራለሁ ብሏል የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ።

አዉሎ ሚዲያ ሰኔ 12/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ