አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው ሪፖርት ሚዛናዊነት የጎደለውና ተቀባይነት የሌለው ነው… የአማራ ክልል መንግስት

0
95

በጎንደርና አካባቢው የተፈጠረውን ግጭትና የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ያወጣውን ሪፖርት ሚዛናዊነት የጎደለው በመሆኑ እንደማይቀበለው የአማራ ክልል መንግስት አስታወቀ።ሪፖርቱ የግጭቱን መንስኤ፣ ችግሩን ለመፍታት የተሄደበትን ርቀትና የመጣውን ውጤት የማያሳይ፤ የአንድን ወገን ፍላጎት መሰረት ያደረገ በመሆኑ ሚዛናዊነት የጎደለውና አድሎአዊ ነው ተብሏል።

የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የቅማንት የራስ አስተዳደር ጥያቄ በህገ መንግስቱ መሰረት ቀደም ሲል ምላሽ ያገኘ መሆኑ የሚታወቅ ነው ብለዋል ።

ይሁን እንጂ የተወሰኑ ጽንፈኛ የታጠቁ ሃይሎች በህወሓት እየተደገፉ የራሳቸውን ፍላጎት ለመጫን በፈጠሩት ግጭት በቅማንትና በአማራ ህዝቦች ላይ ሞት፣ መፈናቀልና ንብረት መውደም መከሰቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው ሲል መግለጫው ያትታል ።

ሪፖርቱ በግጭቱ የቅማንት ማህበረሰብ ላይ ብቻ ጉዳት እንደደረሰ አድርጎ ማቅረቡና የሞቱ፣ የተሰደዱና ንብረታቸው የወደመባቸውን የአማራ ህዝቦችን የረሳ መሆኑ ሚዛናዊናነት የጎደለውና አድሎአዊ ለመሆኑ ማሳያ ነው።

ሪፖርቱ ሲዘጋጅ የአማራ ክልል መንግስት ሃሳብ ያልተካተተበት በመሆኑ፣ በአማራና በኦሮምያ ክልል ላይ በማተኮሩና የክልሉና የፌደራል መንግስታት ችግሩን ለመፍታት የሄዱበትን ርቀትና የመጣውን ለውጥ የሚያሳይ ባለመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርቱን ሲያዘጋጅ ከክልሉ ሰላምና ደህንነት ቢሮ መረጃ አሰባስቤያለሁ ቢልም ቢሮው የሰጠውን ማስረጃ ወደ ጎን በመተው በራሱ ፍላጎት ያዘጋጀው መሆኑን ማረጋገጥ ተችላል ብለዋል።ከዚህ ጋር ተያይዞ በተመሳሳይ ሁኔታ በርካታ የአማራ ዜጎች ከኦሮምያ፣ ቤንሻንጉልና ሌሎች ክልሎች መፈናቀላቸውን እየታወቀ በሪፖርቱ አለመካተቱ የድርጅቱን አድሎአዊ አሰራር ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ መሆኑን በመግለጫው ተጠቅሷል ።ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው ሪፖርት መሰረተ ቢስ በመሆኑ እንደገና እንዲያስተካክል ካልሆነ ግን በክልሉ መንግስት ተቀባይነት እንደማይኖረው ዋና ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል። ዜናው የኢዜአ ነው::

አዉሎ ሚዲያ ግንቦት 24/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ