እየተካሄድ ስላለው ድርድር ሕዝብ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ይገባል አለ – የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት

0
167

በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ የሚያካሂዱትን ድርድር ህዝብ አውቆትና አመኔታ ኖሮት ድጋፉን እንዲያጠናክር በድርድሩ ዙሪያ ያለውን እውነታ ማሳወቅና ግንዛቤ መፍጠር ከመንግሥት እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት አስታወቀ።

የምክርቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም ምክርቤቱ በኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የተለያዩ ተቋማት ተወካዮችን ባሳተፈ ትናንት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለግማሽ ቀን ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ በሁለቱ አገሮች መካከል እየተደረገ ባለው ድርድር ላይ ህዝብ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖረው ተገቢውን መረጃ መስጠትና ማሳወቅ ከመንግሥት ይጠበቃል።

ህዝብ አመኔታ እንዲኖረው ማድረግና አንድነቱን በተለያየ መልክ እንዲገልጽ የማመቻቸት ሥራ መሥራቱ ጠላት እንዳይተባበር የማድረግ አስተዋጽኦ ይኖዋል።

ግብጽ በዲፕሎማሲ ሌላውን ዓለም ለማሳመን ከምታደርገው እንቅስቃሴ ቀድሞ በመገኘት የኢትዮጵያን በዓባይ የመጠቀም መብቷን ማረጋገጥ ይጠበቃል ያሉት አቶ ሙሳ፣ ምክርቤታቸው በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የጀመሯቸውን በጎ የሆኑ እንቅስቃሴዎች ማበረታታት፣ በጉዳዩ ላይ የተሻለ ሀሳብ ያላቸውንም ማሳተፍ ይገባል የሚል እምነት እንዳለው አስታውቀዋል።

‹‹የኢትዮጵያ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግድቡን በተመለከተ ተጨባጭ የሆነ ነገር አድርገዋል የሚል እምነት ባይኖርም ከዛሬ ጀምሮ ግን በምንችለው ሁሉ አቅም ለግድቡ ያለንን ተሳትፎ እንደምናሳይ ቃል እንገባለን›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ሙሳ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለ ልዩነት አንድነቱን አጠናክሮ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ  በፊት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ጉዳዩ በቅርበት እንከታተላለን የሚሉ ባለድርሻ አካላት ግድቡን አስመልክቶ መንግስት ስለ ሚያካሂደው ድርድርም ሆነ የሚይዛቸው አቋም ግልፅ አይደለም ማለታቸው ይታወሳል፡፡

አዉሎ ሚዲያ ግንቦት 20/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ