“ነፍስን ከአደጋ መጠበቅ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው” – ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር እንድሪስ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት

0
125

በዓለም የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ነፍስን ከአደጋ መጠበቅ ሃይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር እንድሪስ አስታወቁ፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር እንድሪስ 1 ሺ 441ኛውን የኢድ አል ፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ትናንት ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ስጋውንም ሆነ ነፍሱን ከኮረና ቫይረስ መጠበቅ ሃይማኖታዊ ግዴታው መሆኑን አስታወቁ፡፡ የእስልምና ሃይማኖት ‹‹ነፍሳችሁን ጥፋት ላይ፤ አደጋ ላይ አትጣሉ ይላል» ያሉት ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ነፍስን አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ የኢድ ሶላት ግዴታ አለመሆኑን አመልክተዋል::

በመሆኑም በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ሙስሊሞች የኢድ ሶላታቸውን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው በቤታቸው ውስጥ መስገድ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ አንድ ሰው ብቻ ሆኖ መስገድ እንደሚቻልም ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ገልጸዋል::

የዘንድሮው የኢድ አልፈጥር በዓል ሁለት ገጽታ እንዳለው የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ መጥፎ ገጽታው፤ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መዘያየር፣ መጠጋጋት እና በመስጊዶች በጋራ ሶላት ማድረግ የማይቻል መሆኑ ነው:: ሌላው አስደሳች ገጽታ ደግሞ ህዝባዊ አንድነት፤ የመንግሥትና የህዝብ መተባበር የታየበት ነው ብለዋል፡፡ በረመዳን ወቅት የነበረው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት በቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቀጥታ ስርጭት መተላለፉን አስታውሰው፤ ለመንግሥት፤ ለመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ከትናንት በስቲያ ለተደረገው የቦታ ርክክብም በራሳቸው እና በሙስሊሙ ማህበረሰብ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

እንደተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ገለጻ፤ የረመዳን ስጦታ ከዕለቱ ቀደም ብሎም ሆነ ከረመዳን በኋላ መስጠት ይቻላል፡፡ የፊጥር ቀን ግን ግዴታ ነው፡፡ ወደ ሶላት ከመወጣቱ በፊት ስጦታው ይሰጣል፡፡ በፊጥር ቀን ስጦታ ካልተሰጠ ፆሙ እንዳልተፆመ ይቆጠራል፡፡ ፆሙ ተቀባይነት እንዲያገኝም ስጦታ መስጠት ይገባል፡፡

ስጦታ የሚሰጠው ወደ ሶላት ከመወጣቱ በፊት የነበረ ቢሆንም በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተለየ አሠራር እንደሚኖረው አመልክተው፤ ማን መስጠት እንዳለበት፣ ለማን መሰጠት እንዳለበት፣ በምን ያህል መጠን እና በምን ሁኔታ መስጠት እንዳለበት በበዓሉ ዋዜማ ለምዕመናኑ በማይክራፎን ትምህርት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

አዉሎ ሚዲያ ግንቦት 16/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ