ባሁኑ ሰአት ተቋማት ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ መጠንቀቅ አለባቸው ተባለ

0
142

ተቋማት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የኢንተርኔት የቀጥታ ግንኙነት/online/ ሥርዓትን በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቀሙ በመምጣታቸው ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢመደኤ/ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ገለፁ፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት ዓለም በሙሉ ትኩረቱን ኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከልና በመቆጣጠር ባደረገበት በዚህ ወቅት ግለሰቦችና ተቋማት ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡

ተቋማት ለቴክኖሎጂ ግንባታ እና ለሌሎች መሠረተ ልማቶች ትኩረት በሚሰጡት ልክ ለሳይበር ደህንነት መረጋገጥም ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

የሳይበር ደህንነት ማስጠበቅ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት ዶ/ር ሹመቴ ግዛዉ ሁሉም ተቋም የሰራተኞቻቸውን የሳይበር ጥቃት የመከላከል አቅምን የማሳደግ እና የደህንነት መጠበቂያ መተግበሪያዎችን ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነነት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ሁነኛ መረጃ ወይም መድሃኒት የሚያቀርቡ በመምሰል ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀሎች በመላው ዓለም እየተፈፀሙ በመሆኑ ህብረተሰቡ የመረጃ ምንጮቹን ተአማኒነት ሳያረጋግጥ በኢ-ሜይል አድራሻ ወይም በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚላኩለትን መልዕክቶች እንዳይቀበል መክረዋል፡፡

ኢመደኤ ወረርሽኙ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ እንደ ሀገር ሲደርግ የነበረውን ጥረት ለማገዝ የተለያዩ አስተዋጽዎችን ማበርከቱን ዋና ዳይሬክተሩ አውስተው በቀጣይም ተቋሙ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት ይሠራል ብለዋል፡፡

ኢመደኤ በአዋጅ የተሰጠውን ተልዕኮ ከመወጣት አኳያ በተለይም በዚህ ወቅት ህብረተሰቡ ተቋማትና መንግስት ለተለያዩ የሳይበር ጥቃቶች ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስቀድሞ ዝግጅት በማድረግ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ዶ/ር ሹመቴ ገልጸዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የአገሪቱን ኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሠረተ ልማትን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አቅም በመገንባት ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ ታስቦ የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡

ምንጭ፡- የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ

አዉሎ ሚዲያ ሚያዚያ 20/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ