የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የቡና ውጭ ገበያ ላይ ጉዳት አላደረሰም ተባለ

0
123

በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት በቀዳሚነት የሚታወቁት አገራት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከባድ የፈተና ምዕራፍ ውስጥ ቢገኙም እስከአሁን ባለው ሒደት ቀውሱ የዘርፉ የውጭ ገበያ ላይ ጉዳት አለማድረሱን ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታወቋል።

የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን የገበያ መረጃና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ኽይሩ ኑሩ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፣ በአሁን ወቅት ኮሮ ቫይረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ከባድ ጫናን እየፈጠረ ይገኛል።

የወረርሽኙ ስርጭትና ሁለንተናዊ ቀውሱም በኢኮኖሚ ልእልና ስማቸው አንቱ የሚባሉ አገራትን ሳይቀር በእጅጉ እየፈተነ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ እንቅስቃሴ እንዲያቋርጡም አስገድዳል።

ዓለም አቀፍ ቀውሱ በተለይ በኢኮኖሚው መስክ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት በውጭ ገበያ ኡደት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች አንዱ በሆነው የቡና ምርት ዋጋ ላይ ጉዳት አልደረሰም፣የዋጋ ቅናሽም አልታየም፣ተጠቃሚ አላጣንም፣ አገራትም ቡናን መረከብ ቀጥለዋል፣ ከሳምንት ቀድሞም ወደ ጣልያን ሳይቀር ቡናንን ልከናል›› ብለዋል።

ቡና የቅንጦት ሳይሆን መሰረታዊ ፍጆታ ከመሆኑ አንፃር አብዛኞቹ አገራት ቡናን መገበያየታቸውን ባያቋርጡም፣ ወረርሽኙ ባስከተለው ሁለንተናዊ ጫና ኮንትራት አራዝሙልን ወይም ሰርዙልን የሚል ጥያቄ የሚያቀርቡ መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በተለይ አንዳንድ አገራት ወደቦችን እየተዘጉ አሊያም ከፍተኛ ዋጋ እየጠየቁ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ስጋት የቡና ገዢዎቹም ሆነ ላኪዎቹ ያላቸውን የሽያጭ ኮንትራት በማሳጠር ግብይቱን ፈጥነው ለማስፈጸም ጥረት እያደረጉ መሆኑንም አብራርተዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱም ከወረርሽኙ ስጋት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ መሰል እክሎች ለመሻገር በተለይ ከፍተኛ ምርት የሚልኩ ላኪዎች ፈጥነው እንዲልኩ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ያስገንዘቡት ዳይሬክተሩ፣ የውጭ ገበያው የአገሪቱ ዋነኛ ደም ስር በመሆኑ ከወረርሽኙ ስጋት ጋር በተያያዘ መንግሥት ሠራተኞች በቤታቸው ሆነው ሥራቸውን እንዲሠሩ ቢወስንም እኛ በሙሉ አቅም እየሠራን ነው›› ብለዋል።

አዉሎ ሚድያ ሚያዚያ 15/20121 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ