የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በቋሚ ህክምና አገልግሎት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው

0
96

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ማርታ በቀለ ቀዶ ህክምና ካደረጉ አንድ ወር ከአስራ አምስት ቀናቸው ነው። ክትትላቸው ሳያበቃ ነበር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ የተከሰተው። ወይዘሮዋም ለወረርሽኙ እጋለጣለሁ በሚል ስጋት ክትትሉን ማቋረጥ መርጠዋል። ከሀኪማቸው ጋርም በስልክ ግንኙነት ለማድረግ ዕድሉ የላቸውም።

እንደ ወይዘሮ ማርታ ሁሉ ወረርሽኙ ያሰጋቸው በወሊድ ክትትል ላይ ያሉት ወይዘሮ እመቤት ታምራት እና ወይዘሮ ሙሉ ጀማል ወረርሽኙም የወሊድ ክትትል ማድረጉም አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል።

በጤና ባለሙያዎች ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲገለገሉ ምክር እየተሰጣቸው ቢሆንም ታካሚው የሚሰጠውን ምክር አክብሮ መተግበር ላይ ክፍተት መኖሩንና ወደጤና ጣቢያ ለመሄድ የሚያሰጋቸውም የሰው የጥንቃቄ መላላት እንደሆነ ያስረዳሉ። በግላቸው የጥንቃቄ ምክሩን እየተገበሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ የወረዳ ሁለት ጤና ጣቢያ ዳይሬክተር ተወካይ ሲስተር ሳምራዊት ግዛው እንደሚሉት ፤ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ እስካለፈው ሳምንት ድረስ ጤና ጣቢያው በቀን ከሚያስተናግደው ሦስት መቶ ታካሚ በግማሽ ቀንሶ ነበር። ታካሚው መቅረቱና ክትትል በሚያስፈልጋቸው ላይ የደረሰው ጉዳት ወደፊት የሚታይ ቢሆንም ችግሩ በሁለት መንገድ የሚገለጥ ነው።

የመጀመሪያው የህክምና ክትትል ያላቸው በማቋረጣቸው በሽታቸው ሊባባስ እና እስከ ሞት ለሚያደርስ ችግር ሊጋለጡ ይችላሉ።

በተለይም የእርግዝና ክትትል አቋርጠው ለወሊድ ብቻ ወደ ህክምና የሚሄዱ ከሆነ ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን ችግር ለመቋቋም ያስቸግራል። ሁለተኛው ደግሞ በወቅቱ በክትትል ያልተፈታ ችግር በህክምና አገልግሎቱ ላይ የሚፈጥረው ጫና ነው።

ለምሳሌ ካለፉት አስር ቀናት ወዲህ ህሙማን እንደ ወትሮ ወደ ጤና ጣቢያው መሄድ ጀምረዋል። ቀጥሮውን ያሳለፈውም የቅርብ ጊዜ ቀጠሮ ያለውም አንድ ላይ መሆኑ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ጫና ተፈጥሯል። ዘገባው የኢ.ፕ.ድ ነው።

አዉሎ ሚዲያ ሚያዚያ 15/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ