የባንኮችን የወለድ መጠን ዝቅ በማድረግ ኮሮና ቫይረስ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅኖ መቀነስ ይቻላል

0
102

ባንኮች የብድር ወለድ ስሌት መጠናቸውን ዝቅ ማድረግ ከቻሉ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እንደሀገር የሚደርሰውን የምጣኔ ሀብት ተጽእኖ ለመቀነስ ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሠሩ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ተናገሩ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ደኑ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ዓለም በአስቸጋሪ የምጣኔ ሀብት ጉዞ ላይ ትገኛለች።

ችግሩ ደግሞ ኢትዮጵያንም የሚጎዳ በመሆኑ የመንግሥት እና የግል ባንኮች የብድር ወለድ መጠናቸውን ዝቅ ቢያደርጉ ኢኮኖሚውን መታደግ እንደሚችሉና የብድር ወለድ መጠንን መቀነስም የኮሮናን ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ ለመቀነስ ከሚወሰዱ አማራጮች መካከል ተመራጩ መንገድም ነው።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ደኑ ገለጻ፤ በበሽታው ስጋት ምክንያት አንዳንዶች እቃዎችን ሲያከማቹ እንደሚስተዋልና ሌሎች ደግሞ የገንዘብ አቅማቸው ዝቅተኛ በመሆኑ እና የሥራ እንቅስቃሴ በመቀነሱ የሚያወጡት ገንዘብ አነስተኛ ስለሚሆን ሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የገንዘብ መጠን ዝቅተኛ ያደርገዋል።

በዚህም ምክንያት ብድር የወሰዱ ሰዎች ሠርተው በፍጥነት ብድራቸውን ለመክፈል እንዲቸገሩ ስለሚያደርጋቸው ባን ኮች የብድር ወለድ መጠናቸውን በመቀነስ ተበዳ ሪዎች እፎይታ እንዲያገኙ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

ባንኮችም በበኩላቸው የሠራተኛ ክፍያ እና ሌሎች ወጪዎችን የሚሸፍኑት ከብድር ወለድ በሚያገኙት ገንዘብ መሆኑን የተናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ የብድር ወለድ መጠኑን ሲቀንሱ ግን የእራሳቸውንም ተቋም ለኪሳራ በማያጋልጥ መልኩ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።

በዚህም ከሁለት በመቶ እስከ ሦስት በመቶ ወይንም እንደ በሽታው ተጽእኖ እየገመገሙ ቅናሽ ቢያደርጉ ለሀገርም የሚበጅ ዕርምጃ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘነበ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በዓለም ላይ የኢኮኖሚ ድቀት ሲመጣ በሀገር ውስጥም የቢዝነስ እንቅስቃሴው ይቀንሳል።

በሽታው ባደረሰው ችግር ደግሞ በርካታ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን ለመቀነስ እንደሚገደዱና ከባንኮች ተበድረው የሚሠሩ አካላትም ብድራቸውን ለመክፈል የሚቸገሩበት ጊዜ ስለሚሆን የብድር ወለድ ስሌት መጠንን ዝቅ በማድረግ ችግሩን መሻገር ይገባል ብለዋል።

ባንኮች ዋነኛ ገቢያቸው የብድር ወለድ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ የሚያስከፍሉትን ወለድ ያንሱ ቢባል የፋይናንስ ዘርፉንም አደጋ ላይ እንደሚጥለው የገለጹት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘነበ የአንድ ሃገር ፋይናንስ ዘርፍ ከወደቀ ደግሞ አጠቃላይ ኢኮኖሚውንም የከፋ ችግር ውስጥ እንደሚከተው ጠቁመዋል። በመሆኑም ባንኮቹ በማይጎዱበት መጠን እራሳቸው ትርፍ እና ኪሳራቸውን እያመጣጠኑ ወለድ ክፍያ ስሌቱን ቢቀንሱ በበሽታው ምክንያት የመክፈል ጫና ውስጥ ለገቡ ተበዳሪዎች የክፍያ ጊዜ እፎይታን ከመስጠቱ በሻገር በኮሮና ምክንያት በሀገር ላይ የመጣውን የምጣኔ ሀብት ችግርንም ለመቅረፍ እንደሚያስችል አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው የዛሬ ሳምንት ኮቪድ- 19ን ለመከላከል የተቋቋመው የማክሮ- ኢኮኖሚ ንዑስ ኮሚቴ የኢኮኖሚው ዘርፉን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አማራጮችን ለመቀየስ ከዐበይት የኢንዱ ስትሪ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ሲያካሂድ መቆየቱን መግለጻቸው ይታወ ሳል።

በዚህም መሰረት ኢኮኖሚውን በማረጋ ጋትና የፋይናንስ ዘርፉን ጤንነት አስጠብቆ ለመቀጠል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ 15 ቢሊየን ብር ለግል ባንኮች እንደሚሰጥ ይፋ አድርገዋል።
ገንዘቡም የግል ባንኮች በኮቪድ-19 ቫይረስ ተጽእኖ ለደረሰባቸው ደንበኞቻቸው ጊዜያዊ የብድር እፎይታ እና ተጨማሪ ብድር ለመስጠት እንዲያስችላቸው የሚውል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ገልጸዋል።


አዉሎ ሚድያ ሚያዚያ 05/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ