የክልሎች ውሳኔዎችና መመርያዎች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር እንዴት ይተገበራሉ?

0
177

በክልሎች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተላለፉ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተጣጥመው እንደሚተገበሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናግረዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለአምስት ወራት የሆነበት ምክንያትም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የስልጣን ጊዜ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ተናግረዋል።

አቶ ንጉሱ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስመልክቶ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በክልሎች የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የተላለፉ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ከወጣው አዋጅ ጋር እንዴት ተፈጻሚ እንደሚሆንም አብራርተዋል።

እንደ አቶ ንጉሱ ማብራሪያ በክልሎች የተፈጥሮ አደጋና የጤና እክል ሲያጋጥም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት እንደሚችሉ በሕገ-መንግስቱ ተደንግጓል።

”ዋናው ጉዳይ የክልሎች አዋጆችና መመሪያዎች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የማይቃረኑ ከሆነ ተጣጥመው ተግባራዊ እንደሚሆኑና የሚቃረኑ ከሆነ ግን የፌዴራል መንግስቱ ያወጣው አዋጅ ተፈጻሚ ይሆናል” ብለዋል።

ክልሎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያሉ መመሪያዎችና ደንቦችን ማጥበቅና ማስፋት እንደሚችሉ ገልጸው፤ ነገር ግን አዋጁን የማላላትና የመከለስ ስልጣን እንደሌላቸው አመላክተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እንደሚችል በሕገ-መንግስቱ ስልጣን የተሰጠው ቢሆንም፤ ምክር ቤቱ የቀረው የስልጣን ጊዜ አምስት ወር በመሆኑ የታወጀው አዋጅ ይህንኑ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል አቶ ንጉሱ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትለው የሚወጡ ደንቦችና መመሪያዎች ከዚህ በፊት የተላለፉ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችን ሊያካትቱ እንደሚችሉም ጠቅሰዋል።

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታትና ለመቆጣጠር ሁሉም የሚመለከተው አካል የጋራ ርብርብ በማድረግ እንዲሁም የበኩሉን ሃላፊነት እንዲወጣም አቶ ንጉሱ ጥሪ አቅርበዋል።


አዉሎ ሚድያ ሚያዝያ 01/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ