ባህር ዳር ከተማ ለኗሪዎቿ የፍጆታ ምርቶችን ቤት ለቤት እያቀረበች ነው

0
393

በባህር ዳር ከተማ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ ኅብረተሰቡ በቤት ውስጥ እንዲቀመጥ በመደረጉ በፍጆታ ምርቶች ላይ የአቅርቦት ችግር እንዳይፈጠር ቤት ለቤት ማቅረብ መጀመሩን የከተማው ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሙሉዓለም ተፈራ ለ ኢዜአ እንደተናገሩት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሲባል ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ኅብረተሰቡ ቤቱ ውስጥ ሆኖ በሽታውን እንዲከላከል ገደብ ተጥሏል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠርና ኅብረተሰቡ ለችግር እንዳይጋለጥ በማሰብ ከመጋቢት 28 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ምርቶችን ቤት ለቤት ማቅረብ ተጀምሯል። ምርቶቹ እየቀረቡ ያሉት በተመረጡ 11 የህብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ሲሆን ቀይ ሽንብኩርት፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ጥቅል ጎመን፣ ድንችና መሰል ምርቶች እየቀረቡ መሆኑን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅትም 350 ኩንታል ቀይ ሽንኩርት ቀርቦ እየተከፋፈለ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስከ አሁን ድረስ በጣና እና ኅዳር 11 ክፍለ ከተሞች 150 ኩንታል ሽንኩርት ለኅብረተሰቡ እንዲደርስ መደረጉን ተናግረዋል። መንግሥት በተመነው መሠረት አንድ ኪሎ ሽንኩርት በ15 ብር ሒሳብ ብቻ እንዲሸጥ እየተደረገ ሲሆን ለጊዜው አንድ ሰው ከአራት ኪሎ በላይ መግዛት እንደማይችልም ጠቁመዋል።

ከማህበራት በተጨማሪም ለስምንት ጅምላ አከፋፋይ ነጋዴዎች ሽንኩርት፣ ማካሮኒና ዘይት ቤት ለቤት እንዲያከፋፍሉ ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሰው አቅርቦቱም መንግሥት ባወጣው ዋጋ እንደሆነ ገልፀዋል። በቀጣይም ጤፍና ፍርኖ ዱቄት ቤት ለቤት እንዲቀርብ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀው፤ ፍላጎቱ ላላቸው ወፍጮ ቤት ባለቤቶች ፈቃድ በመስጠት አስፈጭተው ከቤት የሚያደርሱበት ሁኔታ እንደሚፈጠር አስረድተዋል።


አዉሎ ሚድያ መጋቢት 30/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ