በትግራይ ማእከላዊ ዞን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የተወሰነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተላልፈው የተገኙ ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ተደረገ

0
596

የትግራይ ማዕከላዊ ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ አቶ እያሱ ተስፋይ እንዳሉት  አለአገባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉና ገደብ የተጣለባቸው እንቅስቃሴዎች የጣሱ ከ270 በላይ የንግድ ተቋማት እርምጃ ተወስዶባቸዋል።  

በአክሱም ከተማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ክልከላዎችን የተላለፉና ያለአገባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ግለሰቦች በገንዘብ እና እስራት ተቀጥተዋል ። 

የትግራይ ማእከላዊ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት ባስዋለው ችሎት በአዋጁ  ክልከላ የተደረገባቸውና ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ አድርገው የተገኙ ግለሰቦች በአንድ አመት እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ወስኗል።     

በኮማንድ ፖስት የታሸገ የከረምቡላ መጫወቻ ማዕከል ወረቀቱን ቀዶ በመግባትና በማጫወት የተከሰሰው በአንድ አመት ከሁለት ወር እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ወስኖበታል።

በህገ ወጥ መንገድ በተከፈተው ከረምቡላ ቤት ገብቶ በመጫወቱ ክስ የተመሰረተበት  ሓጎስ ታደለ የተባለ ግለሰብ ደግሞ በስድስት ወር እስራትና አምስት ሺህ ብር እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል። 

ሶስት ሊትር አልኮል በ70 ብር ሒሳብ መሸጥ ሲገባው  በ250 ብር የሸጠ አንድ ግለሰብም በአራት ወራት እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ወስኗል ። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሽታው ለመከላከልና ለመግታት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  ገደብ  የተጣለባቸው እንቅስቃሴዎች ለመተግበር እንደሚሰሩ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአድዋና የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ገልፀዋል ።

የበሽታውን መከሰት ምክንያት በማድረግ  አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ተከታታይና ተገቢ ቁጥጥር በማድረግ እርምጃው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም  የከተማዋ ነዋሪዎች ጠይቀዋል ።

የአክሱም ከተማ ነዋሪ አቶ አሰፋ አባይ በበኩላቸው  በንክኪ የሚተላለፈው የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል መንግስት እየወሰደው ያለው እርምጃ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዋጁ መሰረት ባለፉት ሁለት ቀናት ገበያ እና መሰል ህብረተሰቡ በብዛት የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች እንዲዘጉ መደረጉ የሚደገፍ ውሳኔ ነው ብለዋል።

የህዝብ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የክልሉ መንግስት ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተገቢ እና ወቅታዊ ነው ያሉት ደግሞ በአክሱም ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር ሀጎስ ብርሃነ ናቸው።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በባህሪው የሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች  የሚገድብ በመሆኑ ገደብ በተጣለባቸው እንቅስቃሴዎች ለማስፈጸም የሚደረገው  ጥረት  በጥንቃቄና በሃላፊነት መንፈስ  መተግበር እንዳለበት ጠቁመዋል።

አዉሎ ሚድያ መጋቢት 22/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ