“ህወሓት ሊያቀርብ የሚችለው የሀብት ጥያቄ የለም”- አቶ አወሉ አብዲ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ

0
88

ብልጽግና ያካሄደው ውህደት ህጋዊና በአብላጫ ድምጽ ድጋፍ ያገኘ በመሆኑ ህወሃት ሊያቀርብ የሚችለው የሃብት ጥያቄ የለም ሲል የብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ::

የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወሉ አብዲ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት አሁን ላይ ኢህአዴግ የሚባል ፓርቲ ፈርሷል፤ በእርሱ ምትክ ደግሞ በህጋዊነት ብልጽግና ፓርቲ ተቋቁሟል ስለዚህ ህወሃት ከማዕከል የሚካፈለው ምንም ዓይነት ንብረት የለም::

እንደ አቶ አወሉ ማብራሪያ ህወሃት ከውህደቱ እራሱን አግልሎና ከዚህ በፊት በነበረን የጋራ የስራ ግንኙነት ያፈራናቸው ንብረቶችን የመከፋፈል ጥያቄ አቅርቧል ፤እኛ ወደ ውህደት የመጣነው ህጋዊ አካሄዱን ተከትለንና በአብላጫ ድምጽ ድጋፍ አግኝተን በመሆኑ ህወሃት ሊያቀርብ የሚችለው የሀብት ጥያቄ አይኖርም:: ብልጽግና ፓርቲ ያገኘው አብላጫው ድምጽ ኢህአዴግ የሚባለውን ፓርቲ አፍርሷል፤ ይህ ውሳኔ ደግሞ ያለውን ሀብት የብልጽግና ያደርገዋል:: ከዚህ አንጻር ክልል ላይ ያለ ሃብት ካለ ያንን ይዞ መቀጠል እንጂ የሚካፈለው ነገር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም::

ምርጫ ቦርድ ስለ ሃብት ያስቀመጠው ሀሳብ አለ ያሉት አቶ አወሉ፤ ይህም ቢሆን ግን በእኛ ዘንድ ተቀባይነት የለውም፤ ይህንንም በደብዳቤ አሳውቀናል፤ ለዚህ ዋና ምክንያታችን ደግሞ የፓርቲው መፍረስ በአብላጫ ድምጽ የተወሰነ መሆኑና ጥያቄውም አግባብነት ስለሌለው ነው ሲሉ አስረድተዋል::

ቀድሞም ቢሆን በፕሮጀክት ቢሮና ኢህአዴግ ምክር ቤት ላይ እኩል 45፣ 45 ሆነን ተቀመጥን እንጂ ሀብትን እኩል አላዋጣንም ያሉት አቶ አወሉ፤ እኩል ያላዋጠነው የህዝብ ሀብት እንዴት እኩል እንካፈላለን ሲሉ ይጠይቃሉ? ከዚህ በፊትም ስናነሳ እንደነበረው ፓርቲው ከደጋፊዎች፣ ከአባሎች፣ ከነጋዴዎች እንዲሁም ከሌሎች በተለያየ ጊዜ የተሰበሰበ ሀብት አለው፤ ይህ ሀብት ካልሆነ ለህዝብ መመለስ አለበት እንጂ በግንባር አልያም እራሴን ከውህደት አግልያለሁ በሚል ሰበብ ህወሃት የማይገባውን የሚወስድበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ጠቁመዋል::

አዉሎ ሚድያ መጋቢት 16/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ