ብልጽግና ፓርቲ በትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን ከፈተ

0
127

የብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን በመቐለ ከተማ መክፈቱን አስታወቀ።

የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወሉ አብዲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ ብልጽግና ፓርቲ አገራዊ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን በሁሉም ክልሎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን ከፍቶ እንደሚንቀሳቀስ ቃል በገባው መሰረት የትግራይ ክልል ቅርንጫፉን በመቐለ ከተማ ከፍቷል።

የብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሆነው የተመደቡት አቶ ነብዩ ስሑልሚካኤል በዚሁ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ቀደም ባሉት ጊዚያት ለትግራይ ህዝብ ተጠቃሚነት ሲታገሉ ቆይተዋል፤ አሁን ደግሞ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የመጣውን ብልጽግና ፓርቲ በመቀላቀል የትግራይ ህዝብን ወደ ብልጽግና ለማድረስ ይሰራሉ።

ብልጽግና ፓርቲ ለውጥ የወለደው አገራዊ ፓርቲ ነው ያሉት አቶ ነብዩ፤ አገራዊ ለውጡን አገራዊ ከማድረግ አንጻር ፓርቲው በትግራይ ክልል ጽህፈት ቤት መክፈቱ ተገቢና ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል።

እንደ አቶ ነብዩ ገለጻ፤ ለውጡ መደመርን ይዞ የመጣና ይህ የመደመር እሳቤ ደግሞ ለኢትዮጵያ አንድነት ትልቅ መስዋዕትነት ለከፈለው የትግራይ ህዝብ ብልጽግና ትልቅ እድል ነው።

ህዝቡ ለውጡን ይፈልጋል፤ በምንቀሳቀስበት ወቅትም ከጎናችን እነደሚሆን እናምናለን ያሉት አቶ ነብዩ፤ አላማቸውም ምርጫውን ማሸነፍና ህዝቡን የለውጡ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ብልጽግና በሁሉም ወረዳዎችና ዞኖች ቢሮዎችን በቅርቡ እንደሚከፍትና አደረጃጃቱን እንደሚያሰፋ የገለጹት አቶ ነብዩ፤ ተመሳሳይ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትም በአዲስ አበባ ይኖረዋልም ብለዋል።

አዉሎ ሚድያ መጋቢት 08/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ